ቌንቌ | Language
     
 
መግቢያ ስለ ምርጫ ቦርድ
     
 
Banner

PDF Print E-mail

የኢትዮጵያ ብሔራዊ የምርጫ ቦርድ

ከደርግ መንግሥት መውደቅ ማግሥት የሽግግር መንግሥት የተቋቋመ ሲሆን የሽግግር መንግስቱን ቻርተር መሠረት በማድረግ የምርጫ ኮሚሽን በአዋጅ ቁጥር 11/1984 ዓ.ም ወጣ፡፡ የምርጫ ኮሚሽን በየካቲት ወር 1984 ዓ.ም በወረዳና በቀበሌ ደረጃ የጊዜያዊ አስተዳደር ኮሚቴ አባላት ምርጫ አከናወነ በመቀጠልም በግንቦት ወር 1984 ዓ.ም የብሔራዊ፣ ክልላዊና የወረዳ ምክር ቤቶች አባላት ምርጫ አካሂዷል፡፡

የምርጫ ኮሚሽን ተግባሩን ጨርሶ ሲዘጋ በምትኩ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በአዋጅ ቁጥር 64/1985 ዓ.ም ተቋቋመ፡፡ ቦርዱ ተጠሪነቱ ለኢ.ፌ.ዲ.ሪ የሕዝብ ተወካዮች ም/ቤት የሆነ፣ ከማንኛውም ተፅእኖ ነፃ የሆነና ራሱን የቻለ የምርጫ አስፈፃሚ አካል ነው፡፡  በተሻሻለው የምርጫ ህግ 532/1999 አንቀፅ 6 መሠረት በጠቅላይ ሚኒስትሩ አቅራቢነት በህዝብ ተወካዮች ም/ቤት የሚሾሙ ዘጠኝ አባላት አሉት፡፡ የቦርዱ አባላት ጥንቅር ብሔራዊ ተዋፅኦን መሠረት ያደረገ እና የሴቶችን ተሳትፎ ግምት ውስጥ ያስገባ ሆኖ ከአባላቱ ውስጥ የሕግ ባለሙያ አሉት፡፡ እነዚህም አባላቱ፡-

-    ለህገ መንግሥቱ ታማኝ የሆኑ፣

-    ከፖለቲካ ድርጅት አባልነት ነፃ የሆኑ፣

-    የሙያ ብቃት ያላቸው፣

-    በመልካም ስነ-ምግባራቸዉ የሚታወቁ ናቸው፡፡፡

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በአንድ ዋና ኃላፊና በሁለት ምክትል ዋና ኃላፊዎች የሚመራ ጽ/ቤት ነው፡፡ የጽ/ቤቱ ዋና ኃላፊ ተጠሪነቱ ለቦርዱ ይሆናል፡፡ የቦርዱ ምክትል ኃላፊዎች ተጠሪነታቸው ለዋና ኃላፊው ነው፡፡

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ  ምርጫን በዋናነት የሚያስፈፅሙ በዋና ጽ/ቤትና   በክልል የቅርንጫፍ ጽ/ቤቶች የሚሰሩ በርካታ ቋሚ ሠራተኞች ሲኖሩት በምርጫ ጊዜ ከተለያዩ መንግሥታዊና መንግሥታዊ ካልሆኑ ድርጅቶች የምርጫውን ሥራ የሚያግዙ የምርጫ አስፈፃሚዎች መልምሎ ያሰማራል፡፡  ቦርዱ በአገር አቀፍ ደረጀ 547 የምርጫ ክልሎች እና ወደ 43,500 የሚሆኑ የምርጫ ጣቢያዎች አሉት፡፡

 

ዓላማ

የኢትዮጵያ ብሔራዊ የምርጫ ቦርድ የሚከተሉት ዓላማዎች አሉት፡-

1.  ህገ መንግሥቱን መሠረት በማድረግ ነፃ፣ ገለልተኛና ፍትሃዊ ምርጫ በማካሄድ በህዝብ ድምፅ የተመረጠ መንግሥት እንዲቋቋም ማድረግ፣

2.  ህገ መንግሥቱንና በህግ የተመሰረቱ ተቋማትን የሚያከብሩ የፖለቲካ ድርጅቶች እና ግለሰቦች በእኩልነትና ያለ አድልዎ የሚወዳደሩበት የምርጫ ሂደት መኖሩን ማረጋገጥ፣

3.  ዜጐች በህገ መንግሥቱ በተጐናፀፋት የዲሞክራሲ በተለይም የመምረጥና የመመረጥ መብት በነፃነትና በእኩልነት እንዲጠቀሙ ማድረግ፣

 

የኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ ዋና ዋና ተግባሮች፡-

-    ከማንኛውም የፖለቲካ ወገንተኝነት ነፃ የሆኑ የምርጫ አስፈፃሚዎች ከመራጩ ሕዝብ መካካል እንዲመረጡ ማድረግ፣

-    ህገ መንግሥቱንና የምርጫ ህጉ ሳይሸራረፍ ተግባራዊ እንዲደረግ ለምርጫ አስፈፃሚ አካላት አስፈላጊ ሥልጠናዎችን መስጠት፣

-    ለመራጩ ሕዝብ የሥነ-ዜጋና የመራጮች ትምህርት መስጠት ወይም እንዲሰጥ ማድረግ፣

-    ለምርጫ አስፈፃሚ አካላት አስፈላጊ ደንቦችንና መመሪያዎችን ማዘጋጀትና ማሰራጨት፣

-    በልዩ ልዩ የምርጫ ሂደት ደረጃዎች ለዕጩዎች ምዝገባ፣ ለመራጮች ምዝገባ ለድምፅ አሰጣጥ፣ ለድምፅ ቆጠራና ሪፖርት አቀራረብ የተለያዩ የማስፈፀሚያ ግብአቶችን አዘጋጅቶ ማሰራጨት፣

-    በድምፅ አሰጣጥ ሂደትና በድምፅ ቆጠራ ሂደት የሚከሰቱ የማጭበርበር ተግባሮችን በራሱ ሂደት አጣርቶ ሲያረጋግጥ ድጋሚ ምርጫ እንዲካሄድ ማድረግና፣

-    በአገሪቱ ደረጃ የተካሄዱትን ምርጫዎች ውጤቱን አሰባስቦ ማፅደቅና ለሕዝብ ይፋ ማድረግ ናቸው፡፡

 

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ከ1986 እስከ አሁን ያከናዎናቸው ምርጫዎች

-    በ1987፣ በ1992፣ እና በ1997 ዓ.ም ሦስት ነፃ፣ ፍትሀዊና ዲሞክራሲያዊ በሆነ መንገድ የሕዝብ ተወካዮችና የክልል ም/ቤቶች አባላት ምርጫዎችን ያካሄደ ሲሆን ከዚህ በተጨማሪም የሕገ መንግሥት ጉባኤ አባላት፣ የማሟያ እና የሕዝብ ውሣኔ አካሄዷል፡፡ በአሁኑ ወቅትም 4ኛው አገር አቅፍ ጠቅላላ ምርጫ ለማካሄድ ከፍተኛ ትኩረት በመስጠት ሥራውን እያጠናቀቀ ይገኛል፡፡

 

 

 

ክልላዊ መረጃ

አዳዲስ ዝግጅቶች

ለጊዜው ምንም ዝግጅት አልተገኘም
 


ኮፒራይት © 2010
የኢትዮጵያ ብሔራዌ ምርጫ ቦርድ