ቌንቌ | Language
     
 
መግቢያ ስለ ምርጫ ቦርድ ትምህርትና ስልጠና
     
 
Banner

PDF Print E-mail

ትምህርትና ሥልጠና

 

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ ነፃ፣ ፍትሃዊ፣ ሰላማዊና ዲሞክራሲያዊ ምርጫ እንዲያካሄድ የተቋቋመ ከማንኛውም የፖለቲካ ወገንተኝነት የፀዳ ዲሞክራሲያዊ ተቋም ነው፡፡ ነፃ፣ ፍትሃዊ፣ ሰላማዊና ዲሞክራሲያዊ ምርጫ ለማካሄድ መጠነ ሰፊ ተግባሮችን ከበርካታ ባለድርሻ አካላት ጋር በመተባበር ይሰራል፡፡

የምርጫ ሥራ በቅድመ ምርጫ፣ በምርጫ ጊዜ እና በድህረ ምርጫ ተከፋፍሎ የሚከናወን ፈርጀ ብዙ ተግባር ሆኖ በምርጫ ቦርዱ፣ በቦርዱ ጽ/ቤት ኃላፊዎችና በሠራተኞች እንዲሁም በበርካታ ባለድርሻ አካላት ጥምር ጥረት የሚከናወን ተግባር ነው፡፡ በመሆኑም የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ለጽ/ቤቱ መደበኛ እና ጊዜያዊ ሠራተኞች እንዲሁም ለልዩ ልዩ ባለድርሻ አካላት በምርጫ ሂደት ዙሪያ በርካታ የትምህርትና ሥልጠና ፕሮግራሞችን በልዩ ልዩ ዘዴዎች ይሰጣል፡፡ ትምህርት የሚሰጥባቸው መንገዶችም በግምባር በአሠልጣኞች አማካይነት፣ በቴሌቪዥንና በሬዲዮ ከመገናኛ ብዙሃን ጋር በመተባበር፣ በጋዜጦች ከኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅትና ከልዩ ልዩ የግል ፕሬስ ጋር በመተባበር እና በልዩ ልዩ የህዝብ ግንዛቤ ማዳበሪያ ዘዴዎች በፖስተር፣ በበራሪ ጽሁፎች ... ወዘተ. ትምህርት ይሠጣል፡፡

ትምህርት የሚሰጣቸው አካላት


1. የቦርዱ መደበኛ ሠራተኞች

የቦርዱ መደበኛ ሠራተኞች የሚባሉት የጽ/ቤቱ ኃላፊዎች፣ የክልል ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ኃላፊዎች፣ የልዩ ልዩ መምሪያዎች ኃላፊዎች፣ ኤክስፐርቶች እና ድጋፍ ሰጪ ሠራተኞች ... ወዘተ ናቸው፡፡ እነዚህ ሠራተኞች ከትምህርት ዝግጅትና አሰጣጥ ጀምሮ የቅድመ ምርጫ፣ የምርጫ ጊዜ እና የድህረ ምርጫ ሥራዎችን ከዕቅድ እስከ ትግበራ ድረስ ያለውን ተግባር ያከናውናሉ፡፡ ሠራተኞቹ እንደየሙያቸው ልዩ ልዩ የሥልጠና እና የልምድ ልውውጥ ፕሮግራሞችን ይካፈላሉ፡፡

 

2. የቦርዱ ጊዜያዊ ሠራተኞች

የምርጫ ሥራ በምርጫ ወቅት በርካታ  የሰው ኃይል ያስፈልገዋል፡፡ ጊዜያዊ ሠራተኞችን በሥራ ላይ ያሠማራል፡፡ እነዚህም የምርጫ ክልል ምርጫ አስፈፃሚዎች እና የምርጫ ጣቢያ ምርጫ አስፈፃሚዎች ተብለው የሚታወቁና ምርጫ

በሚያስተባብሩበት ወይም የሚያስፈጽሙበት የአካባቢ ነዋሪዎችና የልዩ ልዩ መንግሥታዊ መ/ቤቶች ሠራተኞች ናቸው፡፡

የቦርዱ ጽ/ቤት በምርጫ ወቅት የዕጩ ተወዳዳሪዎች ምዝገባ እና የመራጮች ምዝገባ እንዲሁም የድምፅ አሰጣጥና የውጤት ቆጠራ ወቅቶችን በመለየት ለክልል ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ኃላፊዎችና ለምርጫ ክልል ምርጫ አስፈፃሚዎች ወይም አስተባባሪዎች  ከመላ አገሪቱ ወደ አዲስ አበባ በመጥራት የገጽ ለገጽ ሥልጠናና ትምህርት ይሰጣል፡፡ ትምህርቱን የሚሰጡት የቦርዱ አባላት፣ የቦርዱ ጽ/ቤት ኃላፊዎች፣ የቦርዱ ጽ/ቤት ከፍተኛ ኤክስፐርቶችና ተጋባዥ ባለሙያዎች ናቸው፡፡

የቦርዱ ጽ/ቤት የገጽ ለገጽ የአሠልጣኞች ሥልጠናና ትምህርት የሚሰጥበት አዳራሽ &የምግብና የመኝታ አገልግሎት ለሰልጣኞች የሚሰጥባቸው ክፍሎች በራሱ ግቢ ውስጥ አደራጅቷል፡፡ የቦርዱ ጽ/ቤት የአሰልጣኞች ሥልጠና የሰጣቸው የቦርዱ የክልል ቅርንጫፍ ጽ/ቤቶች ኃላፊዎችና የምርጫ ክልል የምርጫ አስተባባሪዎች በሥልጠናው ያገኙትን ትምህርት በተዋረድ ወደየአካባቢያቸው ሄደው የምርጫ ጣቢያ ምርጫ አስፈፃሚዎችን ያሰለጥናሉ፡፡

3. ለሌሎች ባለድርሻ አካላት የሚሰጡ ሥልጠናዎች

 

3.1 የህዝብ ታዛቢዎች-

የምርጫ ሥራ ህዝባዊ ሥራ ነው፡፡ ከላይ እንደተገለፀው በርካታ የምርጫ ክልል እና የምርጫ ጣቢያ ምርጫ አስፈፃሚዎች በቦርዱ ይመረጣሉ፡፡ ከእነዚህም በተጨማሪ የምርጫውን ሂደት በመራጩ ህዝብ ስም የሚታዘቡ እና በዕለት ከዕለት የምርጫ ሥራ ክንውን ላይ የሚከሰቱ የመራጩ ሕዝብ  አቤቱታዎችን የሚፈቱ ከየምርጫ ጣቢያው ነዋሪ ህዝብ በጥሩ ስነምግባራቸው የሚመረጡ "የህዝብ ታዛቢዎች" በእያንዳንዱ የምርጫ ጣቢያ አምስት ሰዎች በህዝብ ተመርጠው ይመደባሉ፡፡ እነዚህንም የህዝብ ታዛቢዎች በቦርዱ ጽ/ቤት ሥልጠና ያገኙ የምርጫ ክልል አስተባባሪዎች በተዋረድ ያሰለጥናሉ፡፡

 

3.2 የፖሊስ ኃይል

የፖሊስ ኃይል በዕጩ ተወዳዳሪዎች የምርጫ ዘመቻ ወቅትና በድምፅ አሰጣጥ ወቅት የምርጫ ህጉ፣ ደንቦችና መመሪያዎች በሚያዙት መሠረት የምርጫ ሂደቱ በሰላምና በእርጋታ እንዲከናወን የፀጥታ ማስከበርና የፖሊስ ሚና ምን መሆን እንዳለበት በሚመለከታቸው አካላት ቅድመ ሥልጠና ይሰጣቸዋል፡፡

 

3.3 የፍትህ አካላት

የምርጫ ሂደት በተወሰነ ጊዜ የሚከናወን ተግባር ነው፡፡ በእያንዳንዱ የምርጫ ሂደት ደረጃ የሚከሰቱ አቤቱታዎች በምርጫ ጣቢያና በምርጫ ክልል አቤቱታ ሰሚ ኮሚቴ በተዋረድ ውሳኔ ያገኛሉ፡፡ የምርጫ ክልሉ አቤቱታ ሰሚ ኮሚቴ በሰጠው ውሳኔ የማይስማማ አቤቱታ አቅራቢ አቤቱታውን ወደ መደበኛ ፍርድ ቤት በይግባኝ መልክ ማቅረብ እንደሚችል የምርጫ ህጉ ስለሚፈቅድ አቤቱታዎች በይግባኝ ወደ መደበኛ ፍ/ቤት ይቀርባሉ፡፡ በመሆኑም ፍርድ ቤቶች በይግባኝ የሚቀርቡላቸውን አቤቱታዎች በምርጫ ህጉ የተቀመጡ የይርጋ ሰዓቶችን ጠብቀው አፋጣኝ ውሳኔ መስጠት እንደሚገባቸው በሚመለከታቸው ከፍተኛ የህግ ባለሙያዎች አማካኝነት የምርጫን ጉዳይ ለሚመለከቱ ዳኞችና አቃቤያነ ህግ ሥልጠና ይሰጣል፡፡

 

3.4 ጋዜጠኞች

የምርጫ ጊዜ ብዙ መራጭ ሰለ ፖለቲካ ፓርቲዎች ፖሊሲና ፕሮግራምች አማራጮች ለማወቅ መረጃ የሚፈልግበት ጊዜ ነው፡፡ በዚህ ጊዜ ምርጫን አስመልክቶ ለህዝብ የሚቀርቡ ጋዜጣዊ መግለጫዎች ከስሜታዊነት እና ከወገንተኝነት የፀዱ ሊሆኑ ይገባል፡፡ በመሆኑም ጋዜጠኞች የምርጫ ዜናዎችን እንዴት ሊዘግቡ እንደሚገባቸው በሚመለከታቸው የመስኩ ምሁራን የህግና የምርጫ ባለሙያዎች አማካኝነት ትምህርት ይሰጣቸዋል፡፡

 

3.5 የፖለቲካ ፓርቲዎች

የፖለቲካ ፓርቲዎች ዋነኞቹ የምርጫ ባለድርሻ አካላት ናቸው፡፡ የምርጫ ቦርድ የዕለት ተዕለት የሥራ እንቅስቃሴ ከፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር በመመካከርና በመግባባት ይካሄዳል፡፡ የፖለቲካ ፓርቲዎች ሲደራጁ የህዝቡን ኑሮ ወደተሻለ ደረጃ ከፍ ለማድረግ ለመራጩ ህዝብ ቃል በመግባት ነው፡፡ ስለሆነም ለመራጩ ህዝብ ሰላምና ለአገር ደህንነት ተቆርቋሪና የሰላም አምባሳደሮች ሊሆኑ ይገባል፡፡ በዚህ አኳያ ለፖለቲካ ፓርቲዎች እና ዕጩ ተወዳዳሪዎች ተደጋጋሚ ሥልጠናዎች በራሳቸው ወኪሎች አማካይነት እና በምርጫ ቦርዱ መካከል በሚደረጉ በርካታ የውይይት መድረኮች አማካይነት ይሰጣቸዋል፡፡

 

 

አዳዲስ ዝግጅቶች

ለጊዜው ምንም ዝግጅት አልተገኘም
 


ኮፒራይት © 2010
የኢትዮጵያ ብሔራዌ ምርጫ ቦርድ