ቌንቌ | Language
     
 
መግቢያ ምርጫ በኢትዮጵያ
     
 
Banner

PDF Print E-mail

የምርጫ ታሪክ በኢትዮጵያ


በኢትዮጵያ የምርጫ ታሪክ የተጀመረው በንጉሣዊው/ በዘውዳዊው/ ሥርዓት በአፄ ኃይለሥላሴ ዘመነ መንግሥት ነው፡፡ ዘመኑ በ1911 ዓ.ም ሲሆን ምርጫውን ያከናወነውም ህዝቡ ሳይሆን ንጉሡ  ራሣቸው ከደጃዝማቾችና ከመኳንንቶቹ መካካል የፈለጓቸውን በአማካሪነት እንዲረዷቸው በመምርጥ ነበር፡፡ እነዚህም የንጉሡ አማካሪዎች « የዘውድ አማካሪዎች» ተብለው ሲታወቁ ምክር ቤቱም «የዘውድ ምክር ቤት »በመባል ይጠራ ነበር፡፡

 

ምርጫ በዘውዳዊ ሥርዓት

በ1923 ዓ.ም የመጀመሪያው የተጻፈ ህገ መንግሥት ተረቆ የንጉሠ ነገሥቱን የማይገሰስ ሥልጣንን፣ የዘውድ አወራረስና የፓርላማ ማቋቋሚያ አዋጅ ይዞ በይፋ ወጣ፡፡ በዚህም ህገ መንግሥት ተመሥርቶ የመጀመሪያው ፓርላማ ተቋቋመ፡፡ የፓርላማው ይዘት እኩል የአባላት ቁጥር ያላቸው ሁለት ምክር ቤቶች ማለትም የህግ መወሰኛ ም/ቤት እና የህግ መምሪያ ም/ቤት ተብለው ተቋቁመው ነበር፡፡ ፖርላማዉም ከ1924 እስከ 1928 ሲሰራ ቆይቷል፡፡ የተጠቀሱት ም/ቤቶች አባላትንም የሚመርጧቸው ንጉሠ ነገሥቱ ራሳቸው ነበሩ፡፡ ምክንያቱም በ1923  የተዘጋጀው ህገ መንግሥት ‹‹ህዝቡ ራሱ መምረጥ እስከሚችል ድረስ የምክር ቤቶቹ አባላት በንጉሡና በመኳንንቱ ይመረጣሉ›› የሚል አንቀጽ ስለነበረበት ነው፡፡ ይህ ፖርላማ በጣሊያን ወረራ ምክንያት እስከ 1935 ዓ.ም ድረስ ተዘግቶ ነበር፡፡

ከነፃነት በኋላ በ1935 ዓ.ም የተቋቋመው ፖርላማም እንደፊተኛው የህግ መምሪያና የህግ መወሰኛ  ምክር ቤቶች ነበሩት፡፡ የህግ መወሰኛ ምክር ቤት አባላትም በንጉሠ ነገሥቱ የተመረጡ ሲሆን የህግ መምሪያ አባላት ግን እንደቀድሞው በንጉሡና በባለሟሎቻቸው አማካይነት የተመረጡ መሆናቸው ቀርቶ የአገር የሽማግሌዎች በየወረዳቸው ተሰብሰበው የሚመርጡዋቸው ባላባቶች እንዲሆኑ ተደረገ፡፡ እነዚህ የምርጥ ምርጥ ተወካዮች ከ1935 እስከ 1948 ዓ.ም ድረሰ ሳይለወጡ ለአሥራ አምሥት ዓመታት አገልግለዋል፡፡

ከ1948 ዓ.ም ጀምሮ ህዝቡ ራሱ እንደራሴዎቹን በቀጥታ እንዲመርጥ ተፈቀደ፡፡ ከ1948-1967 ዓ.ም በየአራት ዓመቱ አምስት ተከታታይ ምርጫዎች ተካሂደዋል፡፡ በወቅቱም ምርጫውን የሚያካሂደው የምርጫ ቦርድ የተቋቋመ ሲሆን ከአገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስቴር ጋር በመተባበር ይሰራ ነበር፡፡

የመራጭነት መስፈርቱም ኢትዮጵያዊ መሆን፣ ዕድሜ 21 ዓመትና ከዚያ በላይ፣ በአካባቢው ለአንድ ዓመትና ከዚያ በላይ የኖረ፣ ጤነኛ አእምሮ ያለው የሚል ሲሆን የተመራጭነት መስፈርት ደግሞ ኢትዮጵያዊ መሆን፣ ዕድሜ 25 ዓመት ወይም ከዚያ በላይ፣ ጤነኛ፣ በአካባቢው አንድ ዓመት ወይም ከአንድ ዓመት በላይ የኖረ፣ ሁለት ሺ ብር የሚገመት ተንቀሳቃሽ ንብረት ወይም አንድ ሺ ብር የሚገመት የማይንቀሳቀስ ንብረት ያለው መሆን ነበረበት፡፡

 

ምርጫ በደርግ ዘመነ መንግሥት /1967-1983 ./

ከ4ዐ ዓመታት በላይ አገሪቱን በፈላጭ ቆራጭነት ሲያስተዳድር የቆየውን ዘውዳዊ ሥርዓት በወታደራዊ መፈንቅለ መንግሥት ከሥልጣን እንደተወገደ በጥቂት ወታደራዊ መኮንኖች የተወከለ « ጊዚያዊ ወታደራዊ አስተዳደር ደርግ» በሚል ስም ሥልጣኑን ጨበጠ፡፡ በሥራ ላይ የነበረው ፓርላማ ተበትኖ በምትኩ በ1967 ዓ.ም በጥቅምት ወር ከልዩ ልዩ ወታደራዊ ክፍሎችና መሥሪያ ቤቶች የተውጣጡ 6ዐ ሰዎችን ያቀፈ የመማክርት ጉባኤ ተመሠረተ፡፡ ይህ የመማክርት ጉባኤ እስከ 1968 ዓ.ም ድረስ ሲሰራ ቆይቶ ተበተነ፡፡

በ1979 ዓ.ም 835 አባላት ያሉት የሥራ ዘመናቸውም አምስት ዓመት የሆኑ ባለ አንድ ሸንጎ ምክር ቤት በምርጫ ተሰየመ፡፡ በወቅቱ ለመራጭነት የሚያበቁ መስፈርቶችም፤የመራጭ ዕድሜ 18 ዓመት እና በላይ፣ አእምሮው ጤነኛ፣ በፍርድ ቤት ቅጣት ውስጥ ያልሆነ የሚል  ነበር፡፡

ዕጩውን የሚጠቁመውም፣ የሚያስመርጠው ኢሠፓ/ የኢትዮጵያ ሠራተኞች ፓርቲ ነበር፡፡ ኢሠፓ የመድብለ ፓርቲ ሥርዓትን የሚቃወምና የሶሻሊስት ርዕዮትን የሚከተል ሥርዓት ሆኖ ጠቋሚው፣ አስመራጩ እና ተመራጩ ራሱ  ኢሠፓ ነበር፡፡

 

ምርጫ በሽግግር መንግሥት

ኢ.ህ.አ.ዴ.ግ በትጥቅ ትግል በሥልጣን ላይ የነበረውን አምባገነናዊ መንግሥት ገርስሶ አገሪቱን ከተቆጣጠረ በኃላ ከግንቦት 24-28 ቀን 1983 ዓ.ም በተካሄደው የልዩ ልዩ የፖለቲካ ድርጅቶች ስብሰባ ሰላማዊ የሸግግር  መንግሥት ተመሠረተ፡፡ በሽግግር ወቅቱም እንደ ህገ መንግሥት የሚያገለግል ቻርተር ፀደቀ፡፡ በቻርተሩ መሠረት 86 አባላት ያሉት የተለያዩ የፖለቲካ ድርጅቶች የተሳተፉበት የሽግግር መንግሥት ምክር ቤት ተመሠረተ፡፡ የምርጫ ኮሚሽን ማቋቋሚያ አዋጅ ቁጥር 11/1984 ዓ.ም በሽግግር ወቅቱ ምክር ቤት ተዘጋጅቶ በየካቲት ወር 1984 ዓ.ም የወረዳና የቀበሌ ጊዜያዊ አስተዳደር አካላት ምርጫ ተደረገ፡፡ ብዙ ሳይቆይ በዚሁ ዓመት በግንቦት ወር 1984 ዓ.ም የብሔራዊ፣ ክልላዊ፣ የዞን እና የወረዳ ምክር ቤቶች አባላት ምርጫ ተካሄደ፡፡

 

ምርጫ በኢ...

የኢትዮጵያ ብሔራዊ የምርጫ ቦርድ በህገ መንግሥቱ አንቀፅ 1ዐ2 መሠረት ነፃ፣ ገለልተኛና ፍትሃዊ ምርጫ ለማካሄድ የተቋቋመ ሲቪል ተቋም ነው፡፡

ምርጫ ኮሚሽን ሥራውን አጠናቆ ሲጨርስ በምትኩ ብሔራዊ የምርጫ ቦርድ በአዋጅ ቁጥር 64/1985 ዓ.ም መሠረት ተቋቋመ ፡፡ ቦርዱ ከተሠየመበት ከህዳር 1986 ዓ.ም ጀምሮ የምርጫ አዋጁ አምስት ጊዜ ተሻሽሏል፡፡

 

በዚህም መሠረት፡-

  1. አዋጅ ቁጥር 64/1985 መቋቋሚያው አዋጅ፣
  2. አዋጅ ቁጥር 96/1986 የተሻሻለ ፣
  3. አዋጅ ቁጥር 111/1987 የተሻሻለ ፣
  4. አዋጅ ቁጥር 187/1992 የተሻሻለ ፣
  5. አዋጅ ቁጥር 438/1997 የተሻሻለ ፣
  6. አዋጅ ቁጥር 532/1999 የተሻሻለው የኢትዮጵያ የምርጫ ሕግ፣ ተብለው ይጠራሉ፡፡

የኢትዮጵያ ብሔራዊ የምርጫ ቦርድ ከተቋቋመ ጀምሮ ያካሄዳቸው ጠቅላላ ምርጫዎች፡-

  1. አንደኛው አገር አቀፍ  ምርጫ ግንቦት 1987፣
  2. ሁለተኛው አገር አቀፍ ምርጫ ግንቦት 1992፣
  3. ሶስተኛው አገር አቀፍ ምርጫ ግንቦት 1997 ከዚህ በተጨማሪም ቦርዱ በግንቦት 1986 ዓ.ም የህገ መንግሥት ጐባኤ አባላት ምርጫን እንዲሁም በርካታ የአካባቢ የማሟያ እና  የህዝብ ውሣኔ ምርጫዎችን አካሂዷል፡፡

አራተኛው አገር አቀፍ ምርጫ

አራተኛው አገር አቀፍ ምርጫ በያዝነው ዓመት ግንቦት 15/2ዐዐ2 ዓ.ም  ይካሄዳል፡፡ እስካሁን በተካሄዱት ሦስት አገር አቀፍ ምርጫዎች መራጩ ሕዝብ ስለምርጫ ጠቀሜታና ስለ ዲሞክራሲያዊ መብቶች ልምድና ዕውቀት እንዳዳበረ ይታሰባል፡፡

አራተኛው አገር አቀፍ ምርጫ የሚካሄደው በምርጫ ቦርዱ ዕውቅና ከተሰጣቸው የፖለቲካ ድርጅቶች አብዛኞቹ  የተስማሙበት የሥነ-ምግባር  አዋጁ  በጸደቀ ማግሥት በመሆኑ ከመቼውም ጊዜ ይበልጥ ፍትሃዊ፣ ሰላማዊና ዲሞክራሲያዊ ምርጫ እንደሚሆን ይታመናል፡፡ በመሆኑም መራጩ ሕዝብ በነቂስ ወጥቶ በወቅቱ በመመዝገብ የመምረጥ መብቱን ሊጠቀምበት ይገባል፡፡ ልብ ይበሉ አንድ ካርድ /ድምፅ/ አንድ የምክር ቤት ወንበር ልትሆን ትችላለች ስለዚህ በምርጫው ተሳትፈው ወኪልዎን ይምረጡ፡፡

ምርጫ ተስፋ ነው !!

ምርጫ ራዕይ ነው !!

ጥሩ ራዕይ ያለውን ወኪልዎን ይምረጡ !

 

 

 

ክልላዊ መረጃ

አዳዲስ ዝግጅቶች

ለጊዜው ምንም ዝግጅት አልተገኘም
 


ኮፒራይት © 2010
የኢትዮጵያ ብሔራዌ ምርጫ ቦርድ