ቌንቌ | Language
     
 
መግቢያ ምርጫ በኢትዮጵያ የተሻሻለው የዕጩዎች የምዝገባ ጊዜ
     
 
Banner

PDF Print E-mail

በኢትዮጵያ ብሔራዊ የምርጫ ቦርድ በ2ዐዐ2 ዓ.ም የሚካሄደው

አራተኛው ዙር ጠቅላላ ምርጫ አፈፃፀም የጊዜ ሠሌዳ

የዕጩዎች የምዝገባ ጊዜ መራዘመን አስመልከቶ

የተሰጠ ውሳኔ


በኢትዮጵያ ብሔራዊ የምርጫ ቦርድ ጥር 24 ቀን 2ዐዐ2 ዓ.ም ባካሄደው 112ኛ አስቸኳይ ስብሰባው የተለያዩ የፖለቲካ ድርጅቶች ለእጩዎች ምዝገባ በተሰጠው ጊዜ በበቂ ሁኔታ ተንቀሳቅሰው ከአቅም በላይ በሆነ ምክንያት ዕጩዎቻቸውን ያላስመዘገቡ መሆናቸውን በመግለፅ የዕጩዎች ምዝገባ ጊዜ እንዲራዘምላቸው ያቀረቡትን ጥያቄ በጥሞና እና በጥልቀት መርምሯል፡፡

በዚህም ቦርዱ ባወጣው የምርጫ አፈፃፀም የጊዜ ሠሌዳ አጠቃላይ የምርጫ እንቅስቃሴውን በዕቅዱ መሠረት በአግባቡ እያካሄደ የሚገኝ መሆኑን እና በፓርቲዎቹ የቀረበው የዕጩ ምዝገባ ጊዜ ማራዘም ጥያቄ ማስተናገድ በሚያስከትለው የጊዜ መጣበብ ምክንያት በድምፅ አሰጣጥ አፈፃፀም ዝግጅቱ ላይ ከፍተኛ ጫና ሊፈጥር የሚችል መሆኑን ቢያምንም፣

-    ቦርዱ በ2ዐዐ2 ዓ.ም የሚካሄደውን የጠቅላላ ምርጫ አፈፃፀም የጊዜ ሠሌዳ ረቂቅ ላይ የፖለቲካ ድርጅቶችን ጥቅምት 14 ቀን 2ዐዐ2 ዓ.ም. ባወያየበት ጊዜ በቀረቡት ተመሳሳይ ጥያቄዎች መሠረት በእጩዎች ምዝገባ ሂደት ላይ 1ዐ ቀን መጨመሩን በማስታወስ፣

 

-    በመጪው ጠቅላላ ምርጫ የተሻለ ነፃ፣ ፍትሃዊ፣ ሰላማዊ እና የሕዝብ ተአማኒነት አግኝቶ ሁሉም የፖለቲካ ድርጅቶች ዕጩዎቻቸውን ሙሉ በሙሉ እንዲያስመዘግቡና እንዲወዳደሩ፣ ብቁ ተሳትፎ እንዲያደርጉ፣ በቂ ጊዜ መስጠት እና ለመራጩ ሕዝብ የተለያዩ አማራጮችን በተሟላ መልኩ እንዲቀርብ የሚያስችል መሆኑን በማረጋገጥ፣

ቦርዱ በዛሬው ቀን ባደረገው በ112ኛው አስቸኳይ ስብሰባው የዕጩዎች ምዝገባ ቀን ለተጨማሪ 2ዐ ቀናት እንዲራዘም ወስኗል፡፡ በመሆኑም ጥር 25 ቀን 2ዐዐ2 ዓ.ም. ይጠናቀቅ የነበረው  የዕጩዎች ምዝገባ የካቲት 15 ቀን 2ዐዐ2 ዓ.ም ይጠናቀቃል፡፡

ስለዚህ ተወዳዳሪ የፖለቲካ ድርጅቶች ይህ የጊዜ መራዘም ጉዳይ የመጨረሻ ውሣኔ መሆኑን አውቃችሁ በዚህ ዕድል እንድትጠቀሙ ቦርዱ ጥሪውን ያስተላልፋል፡፡

ስለሆነም በተራዘመው የዕጩዎች ምዝገባ ጊዜ መሠረት የምርጫ አፈፃፀም የጊዜ ሠሌዳው ቀሪዎቹ የምርጫ ክንውኖች ጊዜ እንደተጠበቀ ከዚህ እንደሚከተለው ሆኗል፡፡

 

ተ.ቁ

ክ  ን  ው  ን

ቀ  ን

1

የዕጩዎች ምዝገባ በየምርጫ ክልሉ ጽሕፈት ቤት የሚካሄድበት

ከታህሣሥ 16 እስከ የካቲት

15 ቀን 2ዐዐ2 ዓ.ም.

2

የፖለቲካ ፓርቲዎች የዕጩዎቻቸውን ዝርዝር በግንባር ወይም በፓርቲ ወኪል አማካኝነት ለምርጫ ክልል ጽሕፈት ቤቶች የሚያቀርቡበት፡፡

ከታህሣሥ 16 ቀን እስከ የካቲት

15 ቀን 2ዐዐ2 ዓ.ም.

3

በግል በምርጫ ለመወዳደር ድጋፍ ያሰባሰቡ ሰዎች በቀበሌ መስተዳድር ጽሕፈት ቤቶች ትክክለኛነቱ ተጣርቶ የተሰጣቸውን የድጋፍ ፊርማ በተጠቋሚ ዕጩነት ለመመዝገብ ለምርጫ ክልል ጽሕፈት ቤት የሚያቀርቡበት፡፡

ከታህሣሥ 16 ቀን እስከ የካቲት

15 ቀን 2ዐዐ2 ዓ.ም.

4

በፓርቲም ሆነ በግል ለመወዳደር የቀረበ ማንኛውም ሰው በዕጩነት ከመመዝገብ የሚያግድ ሁኔታ ሲያጋጥመው አቤቱታውን ለምርጫ ክልሉ አቤቱታ ስሚ ኮሚቴ የሚያቀርብበትና ውሣኔ የሚያገኝበት፡፡

ከታህሣሥ 16 ቀን እስከ የካቲት

17 ቀን 2ዐዐ2 ዓ.ም

5

በፓርቲም ሆነ በግል ለመወዳደር ከመመዝገብ የሚያግድ ሁኔታ ያጋጠመው ማንኛውም ሰው አቤቱታውን ለምርጫ ክልል ጽሕፈት ቤት አቅርቦ በተሰጠው ውሣኔ ቅሬታ ካለው ይግባኝ ለክልል ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት አቅርቦ ውሣኔ የሚያገኝበት፡፡

ከታህሣሥ 16 ቀን እስከ የካቲት

2ዐ ቀን 2ዐዐ2 ዓ.ም.

6

የዕጩዎችን ማጣሪያ አልፈው የተመዘገቡ የግል ዕጩዎች የመወዳደሪያ ምልክታቸውን በምርጫ ክልል ጽሕፈት ቤት ተገኝተው የሚመርጡበት፡፡

ከየካቲት 16 እስከ የካቲት

2ዐ ቀን 2ዐዐ2 ዓ.ም.

7

የዕጩዎች ዝርዝር ለየምርጫ ክልሉ ሕዝብ ይፋ የሚደረግበት፡፡

የካቲት 21 ቀን 2ዐዐ2 ዓ.ም

8

የዕጩነት ማረጋገጫ መታወቂያ ካርድ የሚሰጥበት፡፡

ከየካቲት 22 እስከ የካቲት 27 ቀን 2ዐዐ2 ዓ.ም

9

የዕጩዎች የምርጫ ውድድር እንቅስቃሴ በይፋ የሚጀመርበት፡፡

የካቲት 2 ቀን 2ዐዐ2 ዓ.ም.

1ዐ

የዕጩዎች የምርጫ ውድድር እንቅስቃሴ በይፋ የሚጠናቀቅበት፡፡

ግንቦት 12 ቀን 2ዐዐ2ዓ.ም.

ከምሽቱ 12፡ ዐዐ ስዓት

 

ማሳሰቢያ፣

-    መላው የሀገራችን ሕዝብና ተወዳዳሪ የፖለቲካ ድርጅቶች ቀደም ሲል በቦርዱ ይፋ በሆነው የመራጮች ምዝገባ ከጥር 1 እስከ የካቲት 1ዐ ቀን 2ዐዐ2 ዓ.ም. እና የድምፅ መስጫው ቀን ግንቦት 15 ቀን 2ዐዐ2 ዓ.ም. የሚካሄድ መሆኑን እንዲያውቁት፣

 

-    የተራዘመውን የዕጩወች የምዝገባ ጊዜ ተወዳዳሪ የፖለቲካ ድርጅቶች የመጨረሻ መሆኑን አውቃችሁ በአግባቡ በመጠቀም ዕጩ ባላስመዘገባችሁበት የምርጫ ክልል ተንቀሳቅሳችሁ እንድታስመዘግቡ፣

 

-    በየደረጃው የምትገኙ የክልል ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤቶች እና የምርጫ ክልል ጽሕፈት ቤቶችም በተራዘመው የዕጩዎች ምዝገባ ጊዜ ሠሌዳ ዕጩዎችን እየተንቀበላችሁ በህጉ መሠረት በአግባቡ እንድትመዘግቡ ቦርዱ በጥብቅ ያሳስባል፡፡

 

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ

አዲስ አበባ፣

 

 

አዳዲስ ዝግጅቶች

ለጊዜው ምንም ዝግጅት አልተገኘም
 


ኮፒራይት © 2010
የኢትዮጵያ ብሔራዌ ምርጫ ቦርድ