ቌንቌ | Language
     
 
መግቢያ ምርጫ በኢትዮጵያ የምርጫ ስርዓት በኢትዮጵያ
     
 
Banner

PDF Print E-mail

የምርጫ ሥርዓት /System/ በምርጫ አማካይነት የመንግሥት መስተዳድርን የሚያቋቁም አገር የሚከተለው የአመራረጥና የውክልና ዘዴ ነው፡፡

ባሁኑ ጊዜ በአለም አቀፍ ደረጃ 3 የምርጫ ሥርዓቶች /Systems/ አሉ፡፡

እነሱም፡-

  1. የአብላጫ ድጋፍ ሥርዓት /Majority System/
  2. ሚዛናዊ የውክልና ስሌት ሥርዓት /Proportional Representation System/
  3. ድብልቅ ሥርዓት /Mixed System/

ተብለው የሚታወቁት ናቸው፡፡

 

በህገ መንግሥቱ አንቀፅ 56 ላይ በተደነገገው መሠረት በተወካዮች ምክር ቤት አብላጫ መቀመጫ ያገኘ የፖለቲካ ድርጅት ወይም ጣምራ ድርጅቶች የፌዴራሉን መንግሥት የህግ አስፈፃሚ አካል ያደራጃል ወይም ይመራል ይላል፡፡ ህገ መንግሥቱን መሠረት አድርጎ በወጣው የተሻሻለው የሀገሪቱ የምርጫ ህግ አዋጅ ቁጥር 532/1999 አንቀፅ 25 ላይም የምርጫ ሥርዓቱ በአንድ የምርጫ ክልል ውስጥ ከሚወዳደሩ ዕጩዎች መካከል አብላጫ ድምፅ ያገኘ ዕጩ በምርጫው አሸናፊ የሚሆንበት የምርጫ ስርዓት /የአብላጫ ድጋፍ ሥርዓት/ መሆኑ  ተደንግጓል፡፡

የምርጫ አይነቶች

 

በኢትዮጵያ የሚካሄዱ የምርጫ አይነቶች የሚከተሉት ናቸው፡፡

  1. ጠቅላላ ምርጫ፣
  2. የአካባቢ ምርጫ፣
  3. የማሟያ ምርጫ፣
  4. ድጋሚ ምርጫ፣
  5. ህዝበ ውሣኔ ፣

ጠቅላላ ምርጫ

  1. ጠቅላላ ምርጫ በየአምስት አመቱ የሚካሄድ የህዝብ ተወካዮች እና የክልል ምክር ቤቶች አባላት ምርጫ ነው፡፡
  2. ጠቅላላ ምርጫ በመላ ሀገሪቱ በተመሳሳይ ጊዜ ይካሄዳል፡፡ ሆኖም ቦርዱ አስፈላጊ ሆኖ ሲያገኘው እና ጉዳዩ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀርቦ ውሳኔ ሲያገኝ በተለያየ ጊዜ እንዲካሄድ ሊያደርግ ይችላል፡፡
  3. ለፌደራል የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ከአንድ የምርጫ ክልል አንድ ተወካይ ብቻ ይመረጣል፡፡
  4. የክልል ምክር ቤቶች አባላት ቁጥር በየክልሉ ህግ መሠረት የሚወሰን ሆኖ ምክር ቤቶቹ የአባሎቻቸውን ቁጥር ለመቀየር ሲወስኑ ለፖለቲካ ፓርቲዎች በቂ የዝግጅት ጊዜ መሰጠቱን ታሳቢ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል፡፡

የአካባቢ ምርጫ

  1. የአካባቢ ምርጫ በህግ በተደነገገው መሰረት በየደረጃው የሚገኙ የዞን፣ የወረዳ፣ የከተማ፣ የማዘጋጃ ቤት፣ የክፍለ ከተማ ወይም የቀበሌ ምክር ቤት አባላት ምርጫ ነው፡፡
  2. ለአካባቢ ምርጫ በአንድ ምርጫ ክልል ምን ያህል ተወካዮች እንደሚመረጡ እንደየምርጫው አይነትና ለየምክር ቤቱ የሚመረጡትን አባላት መሰረት በማድረግ በየክልሎቹ ህግ ይወሰናል፡፡
  3. የአካባቢ ምርጫ በሚካሄድበት ጊዜ በክልሎች ህግጋት መሰረት ይሆናል፡፡
  4. የአካባቢ ምርጫ ይህንን አዋጅ መሰረት በማድረግ ቦርዱ በሚያወጣው ደንብና መመሪያ መሰረት የሚከናወን ይሆናል፡፡

የማሟያ ምርጫ

የማሟያ ምርጫ የሚካሄደው፡-

  1. በየደረጃው ያሉ ምክር ቤቶች በተለያየ ምክንያት የተጓደሉባቸው አባላት እንዲሟሉላቸው ለቦርዱ ጥያቄ ሲያቀርቡ፣ ወይም
  2. በህጉ መሰረት የቀረበ የይውረድልን ጥያቄ ተቀባይነት ሲያገኝ፣

ቦርዱ ጥያቄው በደረሰው በ3 ወር ውስጥ የማሟያ ምርጫ ያካሂዳል፡፡

 

ድጋሚ ምርጫ

ድጋሚ ምርጫ ከሚከተሉት ምክንያቶች በአንዱ ይካሄዳል፡-

በምርጫ ሂደት የተፈፀመ የህግ መጣስ፣ የማጭበርበር፣ ወይም የሠላምና ፀጥታ ማደፍረስ ድርጊት በስፋቱና በዓይነቱ የምርጫውን ውጤት እንደሚያዛንፍ ከተወዳዳሪ የፖለቲካ ድርጅቶች፣ የግል ዕጩዎች፣ ከታዛቢዎች፣ ከምርጫ አስፈፃሚዎች ወይም ከሌላ ከማንኛውም ምንጭ መረጃ ደርሶት ተጨባጭነቱን በራሱ ማጣራት ሲያረጋግጥ ወይም ተፈፅሟል ብሎ በራሱ ሲያምን ሁኔታውን የመመርመር፣ ውጤቱን የመሰረዝና አዲስ ምርጫ /ድጋሚ ምርጫ/ እንዲካሄድ ያደርጋል፡፡

  • በተሻሻለው የምርጫ ህግ አዋጅ አንቀፅ 76 ንዑስ አንቀፅ 3 መሰረት እጩ ተወዳዳሪዎች እኩል ድምፅ በማግኘታቸው
  • ምክንያት አሸናፊውን መለየት አስቸጋሪ የሆነ እንደሆነ ድጋሚ ምርጫ ይካሄዳል፡፡

 

ድጋሚ ምርጫ ሲካሂድ-

  1. ሌላ አዲስ የመራጮች ምዝገባ ሳያስፈልግ በምርጫ ክልሉ ወይም ችግሩ የተከሰተባቸው የምርጫ ጣቢያዎች ውስጥ ተመዝግበው በነበሩ መራጮች ይካሄዳል፡፡
  2. ከላይ በተጠቀሰው መሰረት ምርጫ እንዲካሄድ ሲወሰን አዲስ የእጩዎች ምዝገባ ሳያስፈልግ ቀድሞ በተመዘገቡ እጩዎች መካከል ብቻ እንዲካሄድ ይደረጋል፡፡
  3. በድጋሚ ምርጫ ወቅት የምርጫ ቅስቀሳ ማድረግ የተከለከለ ነው፡፡

የድጋሚ ምርጫ ዝርዝር አፈፃፀም ቦርዱ በሚያወጣው ደንብ ወይም መመሪያ ይወሰናል፡፡

 

ህዝበ ውሳኔ

ህዝበ ውሣኔ በህገመንግሥቱ መሰረት አግባብ ባለው አካል ሲወሰን የህዝብን ፍላጐት ለመለካት ወይም ለመወሰን ድምጽ የሚሰጥበት ስርዓት ነው፡፡  ህዝበ ውሳኔው እንዲካሄድ የወሰነው አካል በሚሰጠው መመሪያ መሰረት ቦርዱ ህዝበ ውሳኔ ያስፈለገበትን ጉዳይ ለመለየት በሚያስችለው መልኩ የድምጽ መስጫ ጣቢያዎችን በማደራጀት ህዝበ ውሳኔውን ያከናውናል፡፡
 

 

አዳዲስ ዝግጅቶች

ለጊዜው ምንም ዝግጅት አልተገኘም
 


ኮፒራይት © 2010
የኢትዮጵያ ብሔራዌ ምርጫ ቦርድ