|
የመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች በመገናኛ ብዙሃንና የጋዜጠኞች የምርጫ አዘጋገብ ስነምግባር ረቂቅ ደንብ ላይ ተወያዩ። |
|
|
|
|
መጋቢት 29 ቀን 2002
መጪው ጠቅላላ ምርጫ በተሳካ ሁኔታ ይጠናቀቅ ዘንድ የመገናኛ ብዙሃንና የጋዜጠኞች የምርጫ አዘጋገብ የስነምግባር ደንብ አስፈላጊ መሆኑን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የቦርዱ ሰብሳቢ ፕሮፌሰር መርጋ በቃና አስታወቁ።
ቦርዱ በምርጫ ህጉ በተሰጠው ስልጣን መሰረት ለምርጫ ስራ አስፈላጊ የሆኑ ደንቦችንና መመሪያዎችን የማውጣት ስልጣን እንዳለው በማብራራት ይህ የመገናኛ ብዙሃንና የጋዜጠኞች የምርጫ አዘጋገብ የስነምግባር ረቂቅ ደንብን አዘጋጅቶ ለውይይት አቅርቧል ሲሉ የቦርዱ ሰብሳቢ አክለው ተናግረዋል።
የውይይቱ ዓላማ ቦርዱ ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር በመወያየት ለረቂቅ ደንቡ ግብአት የሚሆኑ አስተያየቶችን መቀበልና ለቦርዱ አቅርቦ ማጸደቅ እንደሆነ ተገልጿል።
ውይይቱ መጋቢት 27 ቀን በኢትዮጵያ ብሔራዊ የምርጫ ቦርድ ጽ/ቤት የተካሄደ ሲሆን በውይይቱ ላይ ከመንግስት ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች፣ በአዲስ አበባ የሚገኙ የውጭና የአገር ውስጥ የመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች እንዲሁም የተለያዩ የጋዜጠኞች ማህበራት ተወካዮች ተሳትፈዋል።
በዚህ መሰረት በረቂቅ ደንቡ አንቀፆች ላይ መካተት የሚገባቸውና የማይገባቸው ሃሳቦች ዙሪያ ውይይት የተደረገ ሲሆን ቦርዱም ጠቃሚ የሆኑ የደንቡ ማዳበሪያ ግብአቶች አንደተገኘበት ገልጿል።
ምርጫ ቦርዱ በተሰጠው ስልጣን መሰረት ይህንን ረቂቅ አዘጋጅቶ ለሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋብዞ አስተያየታቸውን በጥሞና ማዳመጡ እንዳስደሰታቸውና መጪውን የ 2002 ምርጫ ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ ለማድረግ የማይተካ ሚና እንደሚኖረው አንዳንድ ተሳታፊዎች ተናግረዋል። |