|
ግንቦት ዐ5 ቀን 2ዐዐ2 ዓ.ም.
አራተኛው ዙር ጠቅላላ ምርጫ በተመለከተ የኢትዮጵያ የኃይማኖት መሪዎች ለተወዳደሪ የፖለቲካ ድርጅት መሪዎች የሠላም ጥሪና ቡራኬ መልእክት በኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ መሰብሰቢያ አዳራሽ በዛሬ ዕለት ሰጥተዋል፡፡
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ክቡር ፕሮፌሰር መረጋ በቃና በመክፈቻ ንግግራቸው እንደተናገሩት ሀገራችን ኢትዮጵያ አሁን በተፈጠረላት ምቹ የዲሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ዕድል መቻቻል፣ መወያየት፣ መፈቃቀር፣ መተሳሰብ፣ ሰላምና ወንድማማችነት በሰፈነበት አኳኃን ሁሉም ዜጎች ያለምንም ልዩነት በመወዳደርም ሆነ በመምረጥ ለዘንድሮው ጠቅላላ ምርጫ ተሳትፏቸው ውጤታማና ለሀገር እድገት የሚበጅ እንዲሆን ክቡራን የሀይማኖት መሪዎቻችን ያላቸውን የሰላም ምኞት እውን ለማድረግ ላለፋት 6 ወራት በሰፊው ሲንቀሳቀሱ መቆየታቸውን አስታውቀዋል፡፡
በዚሁ መሠረት ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳሳ ዘአክሱም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተከለ ሃይማኖት የዓለም አብያተ ክርስቲያናት ምክር ቤት ፕሬዚዳንት የዓለም ሃይማኖቶች ምክር ቤት ለሰላም የክብር ፕሬዚዳንት፣ ሸህ አህመዲን ሸህ አብዱላሂ የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳይ ጠቅላይ ምክር ቤት ፕሬዚዳንት፣ አቡነ ብርሃነየሱስ ሊቀ ጳጳሳት ዘካቶሊካዊያን የኢትዮጵያ ካቶሊካዊያን ጳጳሳት ጉባኤ ፕሬዚዳንት፣ ቄስ ዶ/ር ብርሃኑ ኦፍግአ የኢትዮጵያ ወንጌላዊት ቤት ክርስቲያን መካነ ኢየሱስ ጠቅላይ ፀሐፊ ከቦርዱ ጋር ቀደም ብለው ለዚህ ፕሮግራም መሳካት ትኩረት ሰጥተው አስፈላጊውን ሁሉ ጥረት በማድረግ እነሆ በዛሬው ዕለት ለሀገራችን እና ለመላው ሕዝቦች ዘላቂ ሰላምና እድገት ይበጃል ያሉትን በራሳቸው ተነሳሽነት ለ63ቱ ተፎካካሪ የፖለቲካ ድርጅቶች ሃይማኖታዊ መልዕክት ለማስተላለፍ በቅን ልቦና ከጎናችን በመገኘታቸው ተወዳዳሪ የፖለቲካ ድርጅቶችም ለዚሁ የተቀደሰ የሰላም ጥሪ ተገቢውን አክብሮት በመስጠት በቦታው በመገኝታቸው አመስግናው የኃይማኖት መሪዎች የሚሰጡትን የሠላም ጥሪ በደስታ እንድንቀበልና ሁላችንም በጋራ ተግባራዊ እንድናደርግ ሲሉ ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል፡፡
በመጨረሻም አራቱ የሃይማኖት መሪዎች በበኩላቸው ሰላም፣ መግባባት፣ ፍቅርና ስምምነት ለሁሉም አሰፈላጊ መሆኑን ጠቁመው ለሕዝባችን ጠቃሚ ውጤት ለማምጣት፣ መከባበር፣ መደማመጥ፣ በሰላምና በፍቅር መነጋገርና መወያየት በያንዳንዳችን የሕይወት ገጽታና እንቅስቃሴዎችን ጎልቶ መታየት እንዳአለባቸው በመሳሰብ በሰላማዊ መንገድ መምራት አስተዋይነት ይኖረዋል ብለዋል፡፡ ከዚህ በተቃራኒ ሰላምን የሚያደፈርሱ አላስፈላጊ ሕይወትን የሚያስከፍሉ መፍትሔዎች በእኛ ይብቁ ሲሉ የሃይማኖት መሪዎች ለተወዳዳሪ ፖለቲካ ድርጅቶችና ለመላው የኢትዮጵያ ህዝቦች ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል፡፡
‹‹ኅሡ ሰላማ ለሀገር፤እስመ በሰላመ ዚኣሃ ይከውን ሰላመክሙ››
‹‹ለሀገር ሰላምን ፈልጉ፤ በእርሰዋ ሰላም ለእናንተ ሰላም ይሆንላችኋላና፡፡››
/ኤር 29፡7/
በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን
የ2ዐዐ2 ዓ.ም. አራተኛው ሀገራዊ ምርጫ ፍትሃዊና ሰላማዊ እንዲሆን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ከልብ ትጸልያለች፡፡ ለተወዳዳሪዎችም ሁሉ ‹‹ለሀገር ሰላምን ፈልጉ፤ በእርሰዋ ሰላም ለእናንተ ሰላም ይሆንላችኋልና፤ ስለ እርሰዋም ወደ እግዚአብሔር ጸልዩ›› የሚለውን የእግዚአብሔርን የሰላም መልእክት ታስተላልፋለች፡፡
ስለ ሕዝቦች እድገት፣ ስለ ልማትና ብልጽግና፣ ስለ ፍትሕና የሰው ልጆች እኩልነት፣ ስለ ሀገር ነፃነትና አንድነት፣ ስለ ሕዝቡ የተሻለ ሕይወት፣ የሚደረገው የወንድማማቾች ምኞትና ራእይ ሁሉ በማንም ሆነ በማን ሊሳካ የሚችለው ሰላም መግባባት፣ ፍቅርና ስምምነት ሲኖር ነው፡፡ ለሕዝባችን ጠቃሚ ውጤት ለማምጣት፣ መከባበር፣ መደማመጥ፣ በሰላምና በፍቅር መነጋገርና መወያየት ከሁሉም ይጠበቃል፡፡
ለሕዝብና ለሀገር እንጂ ለራሱ ብሎ ወደ ምርጫ የገባ ስለማይኖር ለሕዝብ ደኀንነትና ለሀገር ሰላም በስከነ መንፈስና አእምሮ መወያየት መልካም ነው፡፡ የሚደረገው ሁሉ በሰላም በርጋታና በትዕግሥት ቢሆን ሕዝቡን የሚጠቅም ውጤት ይገኛል፡፡ ተወዳድሮ ለማሸነፍ፣ ሮጦ ለመቅደም ሰላም ያስፈልጋል፡፡ በአራተኛው ብሔራዊ ምርጫ የሚወዳደሩ ሁሉ ወንድማማቾች ስለሆኑ በወንድማማችነት መንፈስ በመፈቃቀርና በመተማመን እጅ ለእጅ በመያያዝም መወያየት አለባቸው፡፡ በአሁኑ ጊዜ እየተካሔደ ባለው የምርጫ ዝግጅት ችግሮች ሲያጋጥሙ ተወዳዳሪዎች በአንድነት በክብ ጠረጴዛ ተገናኝተው ለመፍታት እያደረጉት ያለው ጥረት ለሰላማችን መጠበቅና ለሕዝባችን ግንዛቤ በእጅጉ የሚጠቅም ስለሆነ ሊበረታታ የሚገባው ነው፡፡
ሀገራችን ኢትዮጵያ ለአህጉራችን የነፃነት ምልክት እንደሆነች፣ የሰላምና የጸጥታም ምልክት ወይም አርአያ መሆን አለባት፣ ይህንም በዚህ ሀገራዊ ምርጫ ወቅት ማረጋገጥና ማስመስከር ይገባል፡፡
ከተማችን አዲስ አበባም የአፍሪካ ኅብረት መቀመጫ እንደመሆንዋ የሰላምና የፍቅር ዋና ከተማ መሆን ስለሚገባት ሁሉም ተወዳዳሪዎች ሰላምን እንዲሹና እንዲከተሉ ያስፈልጋል፡፡ ሁሉም የምርጫው ተወዳዳሪዎች የሚያደርጉት ውይይትና ክርክር በጎ ውጤት እንዲኖረው፣ ውድድሩ ጤናማ እንዲሆን ተገልጋዩ ሕዝብም የሚባለውን ሁሉ በማስተዋልና በተመስጦ መከታተለ እንዲችል ማንኛውም ነገር ከመነቃቀፍ በጸዳ ሁኔታ ገንቢ ሐሳብ በማመንጨትና በማሳየት በመገባባትና በመደማመጥ በጨዋነት መንፈስ ሊካሔድ ይገባል፡፡ አንዱ ሌላውን ካላዳመጣ፣ የሐሳብ ልዩነትም ነውር አለመሆኑን ካልተገነዘበ መግባባት ሊኖር አይችልም፡፡
ስለዚህ ሰላምንና ፍቅርን፣ ትዕግሥትንና ርጋታን የተመላ፣ ፍጹም ወንደማማችነትንና መከባበርን የተላሰበ ውይይት ማድረጉ ተገልጋዩን ሕዝብ ደስ ያሰኛል፡፡
በመሆኑም አስተዋዩ የኢትዮጵያ ሕዝብ ሆይ! ፈሪሀ እግዚአብሔርን ገንዘብ አድርገህ በፍቅርና በሰላም አንድ ሆነህ ፍትሕና ርትዕ የሞላባት፣ የሕዝቦቹ መብትና እኩልነት የተጠበቀባት ሀገርህን ለመገንባት የሚደረገውን ጥረት ሁሉ በንቃትና በማስተዋል መከታተል ይገባሃል፤ ይህ የተጎናጸፍከውን እድል ፈንታ ታላቅ ስለሆነ በመካሔድ ላይ ባለው ሀገራዊ ምርጫ ወሳኙ ሥልጣን ሰጭም ነሽም አንተ ነህ፤ አገልጋዩም ተገልጋዩም አንተ ነህ፤ ስለሆነም ሐቅንና ዕውነትን ይዘህ ግዴታህን መፈጸም ይጠበቅብሃል፡፡
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የሰላም እናት እንደመሆንዋ የሕዝቦች ሁሉ ሰላም እንዲጠበቅ ሰላማዊ ምክርዋን ትለግሳለች፤ የሰላሙ መሪ የክርሰቶስ አካል እንደመሆንዋም ጥላቻ እንዳይኖር፣ የሰላም መልእክትዋን ታስተላልፋለች፡፡
ኳስ ተጫዋቾች ጥሩ ጨዋታ ለማሳየትና ግብ ለማስቆጠር፣ በተመልካችም ዘንድ አድናቆትን ለማትረፍ፣ በመጨረሻም ለሽልማት ለመብቃት ይጫወታሉ፤ ይህም ሊሆን የሚችለው ተጫዋቾቹ የተቀመጠውን ሕግና ሥርዓት ተከትለው ወንድማዊና ሰላማዊ ፋክክር ሲያደርጉ ብቻ ነው፡፡
በዚህ አንጻር ማንኛውም ውድድር በይዘቱ ተመሳሳይነት ስላለው መልካም ውጤት ለማምጣት በተገልጋዩ ሕክዝብ ዘንድም አድናቆትን ለማትረፍ ሰላማዊና ወንድማዊ ውይይት /ክርክር/ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡
ሁላችን እንደምናውቀው በውድድር ዓለም ማሸነፍ ወይም መሸነፍ እንዳለ ግልፅ ነው፤ በመሆኑም ተወዳዳሪዎች ይህን ዕድል ከመገንዘብ ባሻገር ተሸናፊው ውጤቱን በጸጋ ለመቀበል፣ አሸናፊውም የሕዝብን አደራ በአግባቡ ለመወጣት ትሬታም ካለ በሀገሩ ሕግ ለመፍታት ቃል የሚገቡበት ሜዳ እንደሆነ በማመን ውጤቱን ለመቀበል ጠንካራ መንፈስ ያስፈልጋል፡፡
የተራሮች ሁሉ ጫፍ ወደ ላይ ነው›› እንደ ሚባለው የቆየ አነጋገር የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምርጫ ተወዳዳሪዎች ሁሉ ራእይና ፍላጉት አንድን ሀገር ለማሳደግና ለማበልጸግ፣ ያደጉ ሀገሮች ከደረሱበት ለማድረስ፣ ሕዝቡንም በቅንነት ለማገልገል ነው፡፡ ይህም የተቀደሰ ሐሳብ ዕውን ሊሆን የሚችለው ሰላም ሲኖር ነውና ሁሉም ተወዳዳሪ ወገኖች ከማንም በላይ በተገልጋዩ ሕዝብ ክብርና ለሰላም ቅድሚያ ሰጥተው ሊሠሩ ይገባል፡፡ ስለሆነም ሀገራዊው ምርጫ ሰላማዊና ፍትሐዊ ይሆን ዘንድ ሁሉም ‹‹እግዚአብሔር ለሕዝቡና ልባቸውን ወደ እርሱ ለሚመልሱ ሰላምን ስለሚናገር እግዚአብሔር የሚለውን ያዳምጥ››
እግዚአብሔር አምላክ ኢትዮጵያንና ሕዝቦቿን ይጠብቅ እግዚአብሔር አምላካችን ይባርካችሁ፤ ይቀድሳችሁ አሜን!
አባ ጳውሎስ ቀዳማዊ፤
ፓትርያርክ፤ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ፤
ሊቀ ጳጳሳት ዘአክሱም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት፤
የዓለም አብያተ ክርስቲያናት ምክር ቤት ፕሬዚዳንትን፤
የዓለም ሃይማኖቶች ምክር ቤት ለሰላም የክብር ፕሬዚዳንት
በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን፡፡
- ሁሉንም የምትችል እግዚአብሔር አምላካችን ሆይ፣ ሁል ጊዜ ስለምታደርግልን በጎ ነገር ሁሉ እናመሰግንሃለን፡፡
- እግዚአብሔር አምላካችን ሆይ ለሀገራችን ለኢትዮጵያ ፣ለዓለሙ ሁሉ ሰላምህን ስጥልን፤ጽድቅህንም ለሀራችንና ለዓለም ሕዝቦች ሰጣቸው፡፡
- እግዚአብሔር አምላካችን ሆይ፣ ሊካሄድ የታቀደው ሀገራዊ ምርጫ ሰላማዊ ፍትሃዊ እንዲሆን ታደርግ ዘንድ እንለምንሃለን፡፡
- አምላካችን እግዚአብሔር ሆይ፣ አሁን ለሚደረገው ሀገራዊ ምርጫ ለውድድር የቀረቡ የሀገራችን ልጆች ሁሉ ለተገልጋዩ ሕዝብ ደኀንነት፣ ዕድገትና ብልጽግና፣ ለሀገራችን ለኢትዮጵያ ሰላምና ፀጥታ ይሆን ዘንድ፣ በዕውነትና በቅንነት፣ በጥበብና በማስተዋል እንዲወያዩ ትመራቸው ዘንድ እንለምንሃለን፣ እንማልድሃለንም፡፡
- አምላካችን እግዚአብሔር ሆይ፣ ስለ ሀገራዊው ምርጫ በተለያየ ክፍል የሚያገለግሉና የሚሠሩ ኢትዮጱያውያንና ኢትዮጵያውያት ሁሉ ለሀገራቸውና ለሕዝባቸው ሲሉ በተአማኒነትና በኀሊና ዳኝነት፣ ከሁሉም በላይ አንተን በመፍራት እንዲሠሩ ጥበብንና አእምሮን ትሰጣቸው ዘንድ እንለምንሃለን፡፡
- ቅዱስና ቡሩክ ስለሆነው ስምህ ጸሎታችንን ስማ፡፡
ዛሬም ዘወትርም ለዘለዓለሙ አሜን፡፡
አባ ጳውሎስ ቀዳማዊ፤
ፓትርያርክ፤ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ፤
ሊቀ ጳጳሳት ዘአክሱም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት፤
የዓለም አብያተ ክርስቲያናት ምክር ቤት ፕሬዚዳንትን፤
የዓለም ሃይማኖቶች ምክር ቤት ለሰላም ፕሬዚዳንት
ቢስሚላሂ አረህማኒ ረሂማ
በአላህ ስም እጅግ አዛኝና ሩህሩህ በሆነው
ዛሬ ማናቸውም ሰው ስለ ኢስላመ መናገር የማቀናው ቢሆነመ የቃሉን ትክክለኛ ትርጉም ጠንቅቆ የማያውቅ እጅግ በጣም ጥቂት ነው፡፡ ኢስላም ማለት ሰላም ማለት ነው፡፡ ኢስላም ማለት ኃይማኖትና ስላማ መፍጠር የአኗኗር ሥልት ነው፡፡
ይህ መስረታዊ የሃይማኖታችንን መልዕክት በመንተራስ እኛ ኢትዮጵያውያን ሙስሊሞች የአገራችን ሰላም ያሳስበናል፡፡ ሰላም የሕይወት መነሻ ክፍል መሆኑን በያንዳንዳችን የሕይወት ገጽታና እንቅስቅሴ ጎልቶ መታየት እንዳለበት ሃይማኖታችን ያስተምረናል፡፡ አወንታዊ ሰላምን እናበረታታለን፡፡ ነጻነትን ፍትህን የማያጎናጽፈን ሰላም፣ ብሎም በመላው የሰው ዘር መንፈሳዊ ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊና ማህበራዊ መረጋጋት የሚለግሰን ሰላም እንሻለን፡፡ እንደዚህ ዓይነት ሰላምም የዘላላም የአገራችን ገጽታ ሆኖ እንደቀጥል የበኩላችንን ድርሻ እንወጣለን፡፡
አገራችን ኢትዮጱያ በዓለም ላይ የሰላም ተምሳሌት እንደሆነች ዛሬ ሳ ሳይሆን ከዛሬ 14ዐዐ ዓመት በፊት በታላቁ ነቢይ መሐመድ /ሰ.ዐ.ወ/ የተመሰከረላት እንዲህ በማለት ነው፡፡ ‹‹ሐበሻ ውስጥ መልካም ንጉስ አለ፡፡ ከሱ ዘንድ ማንም አይበደልም፡፡ አላህ ካላችሁበት ስቆቃ መውጪያ ቀዳዳ እስኪያበጅላችሁ ወደዚያው ሄደችሁ ብትቆዩ መልካም ነው›› በማለት የሰጡት ምስክርነት ቃል የኢትዮጵያ መሬት የሰላም መሬት እንደሆነች ከመግለጽ አልፎ መሪዎቿም እንደ ንጉስ አስሀማተ ነጀሺ የፍትህና የእኩልነት ዓርማን በማንሳት በ21ኛው ክፈለ ዘመን በመሪዎች ምሳሌነት ሁል ጊዜ ኢትዮጵያ እንድትጠራ የመላው ኢትዮጵያዊያን ሙስሊሞች ምኞት ነው፡፡
ስለዚህ በግንቦት ወር የሚካሄደው አገር አቀፍ ምርጫ ዋና ዓላማው ፍትህ፣ ነፃነትና እኩልነትን በተጠናከረ መልኩ በማስፈን አገራችንን ከድህነትና ኋላ ቀርነት አላቆ ሕዝቧን ወደተሻለ እድገትና ብልፅግና ሊያደርስ የሚችል ፓርቲ የሚመረጥበት ጊዜ ነው፡፡
ስለዚህ የሚዛሄደው ምርጫ አሰተማማኝ ሆነ ሰላምን በመፍጠር የተሻለች አገር መገንባት እስከሆነ ድረስ ምርጫው አሁን ያለንን ሰላም የሚያደፈርስ፣ የሰዎችን ነጻነት የሚገረስስ፣ የሰውን ሕይወት የሚቀጥፍና እየተገነባ ያለውን ልማት የሚያፈርስ የወደፊት የልማት መንገዳችንን የሚዘጋና ለቀጣይ ልማት ሀብት የሆነውን የሰውና የማቴሪያል አቅም የሚያዳክም መሆን እንደሌለበት እንደ ሃይማኖት መሪ ለሁሉም ተወዳዳሪ ፓርቲዎችና ለኢትዮጱያ ሕዝብ ሁሉ ያለኝን መልእክት አስተላልፋለሁ፡፡
እንዲሁም ምኞትና ተስፋችንም ሁሉንም ነገር አላህ /ሱ.ወ./ በሰላም እንዲያጠናቅቅ ፈጣሪያችንን መለመን ነውና ‹‹ አላህ ሆይ አንተ ሰላም ነህ የሰላምም ምንጭ ነህ፣ የልቅናና የልግስና ባለቤት የሆንክው አላህ ሆይ፣ ክብር ለአንተ ይሁን የአገራችንን ሰላምና ብልጽግና አደራ›› በማለት ሁል ጊዜ አላህን /ሱ. ወ/ እንለምናለን፡፡
በመጨረሻም ምንም እንኳን የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ በአመለካከት ብትለያዩም የአንድ አገር ዜጎችና ወንድማማቾች በመሆንናችሁ በመካከላችሁ ያለውን ልዩነት በጸጋ በመቀበል ለአገር ሠላምና ለሕዝቡ ብልጽግና የበኩላችሁን ጥረት ሁሉ በጋራና በሀገር ፍቅር ስሜት እንድታደርጉ በኢትዮጱያዊያን ሙስሊሞች ስም መልዕክቴን አስተላልፋለሁ፡፡ ሰላዳመጣችሁኝ አመሰግናለሁ፡፡
ሸህ አህመዲን ሸህ አብዱላሂ
የኢትዮጱያ እስልምና ጉዳይ ጠቅላይ
ምክር ቤት ፕሬዚዳንት
አራተኛ መደበኛ ብሔራዊ ምርጫ ተወዳዳሪ ፓርቲዎች
"በመካከላቸው ያሉትን ሽማግሌዎች እመክራቸዋለሁ በእናንተ ዘንድ ያለውን የእግዚአብሔርን መንጋ ጠብቁ፤ እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ በውድ እንጂ
በግድ ሣይሆን፤ በበጎ ፈቃድ እንጂ መጥፎውን ረብ በመመኘት ሣይሆን ጎብኙት"
/1ጴጥ.5፡2/
መግቢያ
ከሁሉ አስቀድሜ ይህ ፕሮግራም በመዘጋጀቱ በኢትዮጱያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ስም የተሰማኝን ደስታ ለመግለጽ እወዳለሁ፡፡ "ከችግር መላቀቅ፤ የምግብ ዋስትና ማግኘት፤ቋሚ ሥራ ማግኘት፤ ኃላፊነቶችን ያለ አድሎ መካፈል፤ ከጭቆና ሁሉ ነፃ መሆን፤ ሰብአዊ ክብሮችን ተከብሮ መኖር፤ የትምህርት ዕድል ማግኘት፤ የመኖር ዋስትናው ተጠብቆ መኖር፤ በአጠቃላይ የተሻለ ኑሮ መኖር፤ የኢትዮጵያ ሕዝቦች ምኞት ነው/የሕክቦችን እድገት 6 /፡፡ "እያንዳንዱ ዜጋ መሪዎቹን መምረጥ የራሱ መብትና ኃላፊነት መሆኑን በማወቅ የመምረጥ መብቱን ተጠቅሞ ለሕዝቦች የጋራ ጥቅም አስተዋጽኦ ማበርከት ይጠበቅበታል፤ ለሕዝብ አገልግሎት ራሳቸውን ለመሠዋት እጩ አድርገው የፖለቲካ ሸክም ለመሸከም የሚወዳደሩ ግለሰቦችን በአክብሮት እንመለከታለን"/ ቤተክርስቲያን በዘመናችን 75/፡፡
1. ልዩነቶችን በውይይት መፍታት በተቻለ መጠን በተለያዩ ፓርቲዎች መካከለ ያሉ የምርጫ ልዩነቶችን ለማጥበብ የማያቋርጠ የመግባባት ውይይት ማድረግ ያስፈልጋል ብለን እናምናለን፡፡
2. የኃይል አጠቃቀምን ማስቀረት በምርጫ ወቅትና በኋላ መራጮች ሆኑ ሥነ-ሥርዓት አስከባሪዎች የኃይልና የአመጽ አጠቃቀመን ጨርሶ ማስቀረት፡፡ በአጠቃላይ የሰው ክቡርነት ከሀሳብ ልዩነታችን በላይ መሆኑን አውቀን ለሰላም የሚቸለውን ዋጋ መከፈል ተፈጥሮአዊ ግዴታችን ነው፡፡
3. ያለፈውን ስህተት አለመድገም፡ ወደ ሀገራችን ተጨባጭ ሁኔታ ስንመለስ ላለፋት ብዙ ዓመታት የሀገራችን ሕዝብ የኑሮ ሰላም የሚያናጉ አልፎም ሕይወት እንዲያልፍ ምክንያት የሆኑ ብዙ ዓይነት ግጭቶችንና ጦርነቶችን አስተናግደናል፡፡ እኛ በታሪኩ ውስጥ አልፈን በሁኔታው ያለፍን ሰዎች እነዚያ ጊዜያቶች መልሰን በልጆቻችን ታሪክ ውስጥ ማየት አንመኝም፡፡ ሰላምን የሚያደፈርስ፤ አላስፈላጊ ሕይወትን የሚያስከፍሉ መፍትሔዎች በእኛ ይብቁ፡፡ የበሰለ የሰለጠነና እግዚአብሔርን የሚፈራ ሰው አስተሳሰብና እርምጃ አወሳሰድ ይኑረን በማለት ጥሪያቸንን በኢትዮጵያ ካቶሊካዉት ቤተክርስቲያን ስም እናስተላልፋለን፡፡
4. የመምረጥ ኃላፊነት፡ አሁን ያለንበት ወቅት ለቀጣዩ አምስት ዓመትት የሚመራንን ፓርቲ ለመምረጥ በዝግጅት ላይ እንገኛለን፡፡ የምርጫው ሥነ ሥርዓት በእርግጥ ለአንድ አገር እጅግ አስፈላጊና ሊዘለል የማይችል ጉዳይ ነው፡፡ ሰለዚህም ዕድሜው ለመራጭነት የደረሰ ዜጋ ሁሉ የሀገሪቱ የጋራ ጥቅም ተካፋይ ባለመብት እንደወሆናቸው መጠን የመምረጥም ተፈጥሮአዊ የዜግነት መብትና ኃላፊነት መሆኑን መገንዘብ ያስፈልጋል፡፡ ይህንን መብታችንን በምንጠቀምበት ጊዜ የመጀመሪያውን ደረጃ በሀገራችን ግንባታ ላይ መሳተፋችን በመሆኑ በኀሊናው የወሰነውን ፓርቲ ያለ ምንም ውጫዊ ተጽእኖ መምረጥ ይችላል፡፡
5. ከምርጫ በኋላ ጥንቃቄ ስለማድረግ ከተለያዩ ሀገሮች የምርጫ ሂደት እንደምንማረው፤ የሕዝብ ሰላም የሚቃወሰው በምርጫ ዝግጅት ወቅት ሣይሆን በምርጫ ሂደትና ከምርጫ በኋላ ባሉት ቀናት ነው፡፡ እኛም ካለፋት ጥቂት ልምድ ያየነው ይህንኑ ነው፡፡ ለዚህ ሰላማዊ ውጤት የብዙዎች ተሳትፎ የሚጠይቅ / የመንግሥት የተመራጮችና የመራጮች/ መሆኑ ግልጽ ነው፡፡ ምንም ይሁን ምንም ግን አንዱ በሌላው ላይ በመጠቆም ወይንም ምክንያት በማድረግ የሕዝብን ሰላም ማናጋት አግባብ እንዳልሆነ ለመግለጽ እንወዳለን፡፡ ይህን ስንል ሊባሉ የሚችሉ ምክንያቶች ይኖራል ብለን አናምንም፡፡ ቢኖርም የሰላማዊ ሰውን ሕይወት ለሞት የሚዳርግ አካሄድ መምረጥ ከተፈጥሮ ሕግ የሚቃረን ነው፡፡
6. ጸሎት ስለማድረግ፡ በምርጫ ጉዳይ ዙሪያ እያንዳንዱ የኢትዮጵያ ሕዝብና የሚመለከተው ክፍል ሁሉ ምርጫው ሰላማዊና የተሳካ እንዲሆን የሚቻለውን ጥረት እንዲያደርጉ በእግዚአብሔር ስም አደራ እያልኩ፤ ምእመናን ሁሉ ምርጫው በሰላም እንዲጠናቀቅ ጸሎት እንዲያደርጉ ለማሳሰብ እወዳለሁ፡፡
እግዚአብሔር ኢትዮጵያን ይባርክ፡፡
ጸሎት
ጊታ ሆይ የሰላም መሣሪያ እንድሆን አድርገኝ
ጥል ባለበት ፍቅር
በደል ባለበት ስምምነት
ጥርጣሬ ባለበት እውነት
ተስፋ መቁረጥ ባለበት መጽናናት
ሐዘን ባለበት ደስታ
ጨለማ ባለበት ብርሃን እንዲገኝ አድርግ
ዘንድ አብቃኝ!ሜን!
+ አቡነ ብርሃነየሱስ
ሊቀ ጳጳሳት ዘካቶሊካዊያን
የኢትዮጵያ ካቶሊካዊያን ጳጳሳት ጉባኤ ፕሬዚዳንት
4ኛውን ሀገር አቀፍ ምርጫ በተመለከተ ከኢትዮጵያ ወንጊላዊት ቤተ ክርስቲያን ወካነ ኢየሱሰ የተላለፈ መልእክት
ግንቦት 5 ቀን 2ዐዐ2 ዓ.ም.
አዲስ አበባ
በሰመ አብ፣ በሰመ ወልድ፣ በሰመ መንፈስ ቅዱስ፣ አንድ አምላክ፣ አሜን
የኢትዮጰያ ወንጌላዊት ቤተ ክርስቲያን መካነ ኢየሱስ በሀገር አቀፍ ከተመሠረተችበት ጊዜ አንስቶ መሪዎቸዋን የምትስይመው በምርጫ ነው፡፡ ምዕመናን በእየአራት ዓመቱ ተሰባስበው ለመጪው አራት ዓመታት የሚመሩዋቸውን መሪዎች በስውር ድምጽ አሰጣጥ ከመረጡ በኋላ ኃላፊነቱን ስጥተው ወደ ቦታቸው ይመለሳሉ፡፡ በመሆኑም ምርጫ ለቤተክርስቲያናችን ዛሬ የተጀመረ አዲስ ነገር አይደለም፡፡ ጠቀሜታውም የላቀ እንደሆነ እንረዳለን፡፡
እግዚአብሔር ከፈጠራት ዓለም ውስጥ ለእኛ የተሰጠቸን ሀገር ኢትዮጵያ ናት፡፡ ይህችን ሀገር ዛሬ ካለችበት ደረጃ ለማድረስ ፣ በዚህም ዘመን ላለን ዜጎች ለማስረከብ አባቶችና እናቶች በየጊዜው ውድ ዋጋ ከፍለዋል፡፡ በሺዎች የሚቆጠሩ ወገኖችም መተኪያ የሌላትን ሕይወታቸውን ሳይቀር ሰጥተው በእነሱ ሞት እኛ ልጆቻቸው ባለሀገር እንድንሆን አድርገው አልፈዋል፡፡ በመሆኑም የዘር፤ የነገድ፤ የቋንቋ የጾታና የሃይማኖት ልዩነት ሳይኖር የሁላችን የሆነች፤ የእኛ የምንላት ሀገር ኢትዮጵያችን ናት፡፡
ለመጪው ትውልድም የምናስረክበው ይህችኑ ሀገር ነው፡፡ ሰለዚህ በሚገባ ጠብቀን ዛሬ ከደረሰችበት ዕድገት ወደ ላቀ ደረጃ በማድረስ ለልጆቻችንና ለልጅ ልጆቻችን የበለጸገች ኢትዮጵያ ለማስረከብ የሰላም መሰፈን እንዲሁም የፍትህ መጎልበትና የዴሞክራሲ ሥር መሰደድ አስፈላጊነት አጠያያቂ አይደለም፡፡ ለዚህም በሰላማዊ መንገድ እንቅስቃሴዎችን መምራት አስተዋይነት ነው፡፡
መጽሐፍ ቅዱስ «ሰላምን እሻ ተከተላትም »መዝ./34/፡14 እንዳለው ልንከተለው የሚገባ ሰላምና ሰላም ብቻ መሆኑን ሁላችንም አንዘነጋውም፡፡ ሰላም ሁላችንንም ተጠቃሚ ያደርገናል፡፡ ከሰላምም በሰተቀር ሌላ አማራጭ የለንም፡፡ በመሆኑም ወደ ከፍተኛ የመንግሥት ኃላፊነት ወይም ሥልጣን ለመውጣት የሕዝቡን የሁንታ በማግኘት ብቻ ሊሆን ይገባል፡፡ ይህም የሕዝብን የበላይነት የሚያረጋግጥ ከመሆኑም በላይ በሀገራችን ፈጣን ዕድገት ለማስገኘትና ሕዝባችንን አንቆ ከያዘው ድህነት ለማላቀቅ ለሚደረገው ጥረት ጠቀሜታው ከፍተኛ ነው፡፡
እንግዲህ መጭው ሀገር አቀፋዊ ምርጫ በሰላማዊ መንገድ እንዲከናወን ሁሉም ፓርቲዎች የራሳቸውን ኃላፊነት በብቃት መወጣት ይጠበቅባቸዋል፡፡ ሌሎች ሀገሮች በሰላማዊ መንገድ ተግባራቸውን ማከናውን ከቻሉ እሃ የማንችልበት ምክንያት አይኖርም፡፡ ስለዚህ በስከነ መንገድ ሁኔታዎችን በመምራት ለሕዝብ ያላችሁን ተቆርቋሪነት በተግባር ልትገልጹ ይገባል፡፡ ለሕዝብ መብት የቆመ ፓርቲ ወይም ግለሰብ እውነተኛ መገለጫው ተግባሩን በሰላማዊ መንገድ ማከናወኑና የሕዝብንና የሀገርን ጥቅም ማስቀደም መቻሉ ነው፡፡
ህዝቡም የሚፈልገውንና ይጠቅመኛል ያለውን በሰላማዊ መንገድ በመምረጥ ኃላፊነቱን መወጣት ይጠበቅበታል፡፡ የዚህች ሀገር ባለቤት ህዝቡ ራሱ ነውና፡፡ በተለይም ወጣቱ ትውልድ ነገ በኃፊነት የሚረከባትና የሚመራት ኢትዮጱያ ፍትሕ፣ እኩልነት ሰላምና ዲሞክራሲ የሰፈነባት ትሆን ዘንድ ዛሬ ማስተዋልና ጥንቃቄ በተሞላው ሁኔታ መንቀሳቀስ ይገባዋል፡፡
አራተኛው አገር አቀፍ ምርጫ የተዋጣለት እንዲሆንና በሰላም ተጀምሮ እንዲጠናቀቅ በተለይም የፓርቲ መሪዎችና እጩ ተወዳዳሪዎች ታሪካዊ ኃላፊነታችሁን እንድትወጡ አደራችን የጠበቀ ነው፡፡ ሁላችንም የሚጠበቅብንን ካከናወንን መጭው ምርጫ አንድ ታላቅ ታሪክ ለማስመዝገብና ለተተኪው ትውልድ ብርቱ መልእክት ለማስተላለፍ የምንችልበት መልካም አጋጣሚ ይሆንልናል፡፡ ስለሆነም ነገ ትውልዱ የሚማርበትና እኛም የምንደሰትበት አዲስ ታሪክ የምንሠራበት ጊዜ እንዳያልፈን ሁላችንም በአንድነት የዜግነት ኃላፊነታችንን እንድንወጣ ቤተ ክርስቲያናችን በአጽንኦት ታበረታታለች፡፡
ሰላም የሰፈነባት ልጆቻችን በሰላም ነፃና ሰላማዊ ምርጫ መሪዎች ኃላፊነት የሚረከቡበትን ሥርዓት የዘረጋችና የበለጸገች ኢትዮጵያን ለመጭው ትውልድ ለማስረከብ ቆርጠን እንነሣ፡፡
በመጨረሻም ምርጫው በሰላማዊ መንገድ እንዲጠናቀቅ ቤተ ክርስቲያን በጽሎት ከጎናችሁ እንደምትቆምና ምዕመናንም ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ በብርቱ እንደምታሳስብ ለመግለጽ እንወዳለን፡ እንዲሁም ለሰላም ከሚደክሙ ጋር የሚቻለውን ሁሉ ከማድረግ የማንቆጠብ መሆናችንን ስንገልጽ በታላቅ አብክሮት ነው፡፡
እግዚአብሔር ሀገራችንን ይባርክ ይጠብቅ፣
እግዚአብሔር ፈቱን ያብራልን ለህባችንም ጸጋው ይሰጥ፣
አግዚአብሔር ፈቱን ለሀገራችን ያንሳ ስላሙንም ያብዛል፣
ሁሉን ቻይ የሆነው እግዚአብሔር ኢትዮጵያን ይባርክ አሜን፡፡
ደረጃ ጀምበሩ
የኢትዮጵያ ወንጌላዊት ቤት ክርስቲያን
መካነ ኢየሱስ ምክትል ፕሬዚዳንት |