ቌንቌ | Language
     
 
መግቢያ ዜና ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የተሰጠ ጋዜጣዊ መግለጫ
     
 
Banner

ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የተሰጠ ጋዜጣዊ መግለጫ PDF Print E-mail

ግንቦት 14 ቀን 2002 ዓ.ም.

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በመላው ሀገሪቱ አራተኛውን ዙር ጠቅላላ ምርጫ በነገው ዕለት ያካሂዳል፡፡ ምርጫውን ለማካሄድ አስፈላጊው ዝግጅት በተሳካ መልኩ ተጠናቋል፡፡  ለድምፅ አሰጣጡ የሚያስፈልጉ ሰነዶችና የምርጫ ማስፈፀሚያ ቁሳቁሶች በበቂ ሁኔታ በሁሉም የሀገሪቱ ክፍሎች በሚገኙ የምርጫ ጣቢያዎች በወቅቱ ደርሷል፡፡  መላው የሀገራችን መራጭ ሕዝብ በነፃነት ወጥቶ ድምፁን ለመስጠት ዕለቱንና ሰዓቱን በጉጉት በመጠባበቅ ላይ ይገኛል፡፡ በመሆኑም ማንኛውም አካል ይህንኑ መሠረት በማድረግ #ትልቅ ክብር ለሕዝብ ድምፅ$ መስጠት ይኖርበታል፡፡

ድምፅ አሰጣጥ ሂደቱ ሰላማዊ በሆነ መልኩ እንዲከናወን እና መራጩ ሕዝብ በተፈጠረለት ምቹ ሁኔታ በነፃነት የሚፈልገውን መርጦ ወደ መደበኛ ዕለታዊ ፕሮግራሙ መሄድ ይችል ዘንድ የሁሉንም ወገኖች ድጋፍ ይፈልጋል፡፡  በነገው ዕለት የምረጡኝ ቅስቀሳ ምልክቶችንም ሆነ መልዕክቶችን ለብሶ ወይም በማንኛውም መልኩ ይዞ ወደ ምርጫ ጣቢያ መግባት አጥብቆ የተከለከለ ነው፡፡ በመሆኑም ይህን ድርጊት ፈፅሞ የተገኘ አግባብ ባለው ሕግ ተጠያቂ መሆኑን ከወዲሁ መገንዘብ ያስፈልጋል፡፡

ማንኛውም ዓይነት የምርጫውን ሂደት የሚጎዳ ይዘት ያለው መሣሪያ፣ ቁሳቁስ፣ ማስመሰያ የምርጫ ሰነድ ይዞ በምርጫ ጣቢያ አካባቢ ወይም ይዞ ገብቶ የተገኘ ሰው በዲሞክራሲ ሂደቱ ላይ የሚጥለው ጠባሳ ከባድ ስለሆነ በዚህ ጉዳይ ቦርዱ  ተገቢውን ክትትል ሁሉ በማድረግ ሕጋዊ እርምጃ የሚወሰድ መሆኑን በቅድሚያ ያሳስባል፡፡

ይህም ሲባል ምርጫው ነፃ ፍትሐዊ፣ ሰላማዊና ዲሞክራሲያዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ ቦርዱ ምቹ ሁኔታ የፈጠረ ከመሆኑም በላይ መራጩ ሕዝብ በነቂስ ወጥቶ ይበጀኛል የሚለውን ለመምረጥ በሙሉ ልብ መዘጋጀቱን በተለያዩ ሚዲያዎች አረጋግጧል፡፡

ስለዚህ ማንኛውም አካል የሕዝብን ሉአላዊ ድምፅ ማክበር እንዳለበት አሁንም  በድጋሚ ጥሪያችንን እናቀርባለን፡፡  በየትኛውም ዲሞክራሲያዊ ምርጫ በሚካሄድባቸው ሀገሮች የሕዝብ ውሣኔ የበላይ ብይን መሆኑና በማንኛውም አካል የተከበረ መሆኑ በተግባር የተረጋገጠ ነው፡፡

በአጠቃላይ መራጩ ሕዝብ በነገው ዕለት ከማለዳው 12፡00 ሰዓት ጀምሮ እስከ ምሽቱ 12፡00 ሰዓት በየተመዘገበበት የምርጫ ጣቢያ ብቻ የተመዘገበበትን ካርድ ይዞ በግንባር በመገኘት ህገመንግሥቱ የሰጠውን መብት ተጠቅሞ ድምፁን ለሚፈልገው ፓርቲ እና ዕጩ በነፃነት እንዲሰጥ የከበረ ጥሪያችንን እናስተላልፋለን፡፡  የተወዳዳሪ የፖለቲካ ፓርቲዎችም በዕለቱ የመራጩን በነፃነት ድምፅ የመስጠት መብት ከሚጋፋ እና በሕግም ከሚያስጠይቅ ከማንኛውም የቅስቀሳ ድርጊት አባላቶቻቸውና ደጋፊዎቻቸው እንዲቆጠቡ ማድረግና ወኪሎቻቸውም በየተመደቡበት የምርጫ ጣቢያ ከማለዳው 10፡30 ጀምሮ እንዲገኙና ሂደቱን እንዲከታተሉ አጥብቀው እንዲያሳስቡልን የከበረ ጥሪያችንን እናስተላልፋለን፡፡

 

ቦርዱ በተሻሻለው የኢትዮጵያ የምርጫ ሕግ አዋጅ በተሰጠው ሥልጣን መሠረት የምርጫውን ውጤት ከግንቦት 16 ቀን 2002 ዓ.ም. ጀምሮ በጊዜያዊነት ይፋ ያደርጋል፡፡ መላው የሀገራችን ሕዝብ ይህንኑ ተገንዝቦ ጊዜያዊ ውጤቱን በአንክሮ እንዲከታተል ጥሪያችንን እናስተላልፋለን፡፡

በመጨረሻም የመራጩን ሕዝብ ብይን ለሕግ ተገዢ ሆነው በፀጋ መቀበልና ለመጪው አምስት ዓመት በሕዝብ ድምፅ በማሸነፍ ለቀጣዩ አምስት ዓመት ሀገሪቷን ከሚመራው መንግሥት የሚመሠርት የፖለቲካ ድርጅት ጋር ተባብሮ ለመስራት ከወዲሁ እራሳቸውን ዝግጁ ማድረግ፤ ቅሬታም ካለ በሀገሪቱ ሕጎችና ቦርዱ ባወጣው በየደረጃው የሚቋቋም አቤቱታ ሰሚ ኮሚቴ አደረጃጀትና አሠራር ደንብ መሠረት አቅርቦ መፍትሔ ሊያገኝ እንደሚችል ለተወዳዳሪ የፖለቲካ ፓርቲዎችና ለመላው የሀገራችን ሕዝብ እናረጋግጣለን፡፡

 

 

አዳዲስ ዝግጅቶች

ለጊዜው ምንም ዝግጅት አልተገኘም
 


ኮፒራይት © 2010
የኢትዮጵያ ብሔራዌ ምርጫ ቦርድ