|
በዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ላይ ውይይት ተደረገ። |
|
|
|
|
መጋቢት 3 ቀን 2003 ዓ.ም
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ከጽ/ቤቱ ሠራተኞች ጋር በዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ዙሪያ ለአንድ ቀን በተቋሙ የሥልጠና ማዕከል ውይይት አካሄደ።
የቦርዱ ሰብሳቢ ፕ/ር መርጋ በቃና በውይይቱ መክፈቻ ላይ እንደገለጹት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በህገ-መንግስቱና በምርጫ ህጉ የተጣለበትን ተግባርና ኃላፊነት በብቃትና በታማኝነት ለመወጣት የሚችለው መላው የጽ/ቤቱ ሠራተኞች አገሪቱ የምትመራበትን ፖሊሲና የትኩረት አቅጣጫዎች ጠንቅቀው ሲያውቁ መሆኑን በማስገንዘብ፣ መንግስት በቀጣይ አምስት አመት ሊተገብራቸው ያቀዳቸውን
የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ተግባራትና ዋና ዋና የትኩረት አቅጣጫዎችን ለሠራተኛው በማሳወቅ ቦርዱ ከተቋቋመበት ዓላማ አንፃር እየቃኘ ወደ ተግባር እንዲለውጠው በማሰብ ይህ የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረክ መዘጋጀቱን ጠቁመዋል።
በቀጣይም የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረኮች በማዘጋጀት ያሉብንን ክፍተቶች በመፈተሽና በማየት እያጠናን ወደፊት ተጠናክረው የሚሰጡ መሆኑንና እያንዳንዱ ሠራተኛ የሚያከናውነውን ሥራ ከዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ጋር እየቃኘ ወደ ተግባር እንዲገባ አሳስበዋል።
ቦርዱም በቀጣይ የአምሰት ዓመቱ ስትራቴጂክ ዕቅድ ላይ ከመ/ቤቱ ሠራተኞች ጋር ውይይት በማድረግ ጠቃሚ አስተያየቶች እንዲካተቱ አድርጓል። በውይይቱ ላይ 89 ሴቶች እና 121 ወንዶች በጠቅላላው 210 የጽ/ቤቱ ሠራተኞች የተገኙ መሆናቸው ለማወቅ ተችሏል። |