|
ሰኔ 6 ቀን 2003 ዓ.ም
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ለፖለቲካ ፓርቲ መሪዎች ከሰኔ 6 እስከ ሰኔ 10 ቀን 2003 ዓ.ም ለ5 ቀናት ትራንስፎርሜሽናል ሊደርሽፕ ላይ ቢሾፍቱ በሚገኘው የኢትዮዽያ ሥራ አመራር ማሠልጠኛ ተቋም ስልጠና መስጠት መጀመሩን የጽ/ቤቱ ምክትል ዋና ኃላፊ ወ/ሮ ራሄል ታደሰ አስታወቁ፡፡
ምክትል ዋና ኃላፊዋ እንደገለፁት የስልጠናው ዋና አላማ የፖለቲካ ፓርቲዎችን አቅም በመገንባት በሃገራችን የተጀመረውን የዲሞክራሲ ሂደት ይበልጥ ለማጠናከርና ወደተሻለ ደረጃ ለማድረስ ነው ብለዋል።
ቦርዱ ቀደምሲል በተለያዩ አበይት ጉዳዩች ዙሪያ ለፖለቲካ ፓርቲ ከፍተኛ አመራሮች ተከታታይነት ያለው የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረኮችን ሲያዘጋጅ መቆየቱን ኃላፊዋ አስታውሰው ለወደፊትም በተመሳሳይ አበይት ሀገራዊ ጠቀሜታ ባላቸው ሌሎች ስልጠናዎችን እንደሚያዘጋጅ በተጨማሪ ጠቁመዋል።
ሥልጠናው ቦርዱ በ2ዐዐ3 ዓ.ም በያዘው የአቅም ግንባታ የስልጠና እቅድ መሰረት የመጀመሪያ ዙር ሥልጠና መጀመሩ እና ሁለተኛው ዙር ስልጠና በቅረብ ቀን እንደሚሰጥ ለማወቅ ተችሏል።
በሥልጠናው ላይ በቦርዱ ህጋዊ እውቅና ካገኙ ከሁሉም ፖለቲካ ፓርቲዎች የተወከሉ በጠቅላላው 76 ሰልጣኞች በሁለት ዙር የሚሰለጥኑ ሲሆን የመጀመሪያ ዙር 40 እና ሁለተኛው ዙር 36 የፖለቲካ ፓርቲ ኃላፊዎች እንደሚሳተፉ ታውቋል፡፡
በኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ህጋዊ እውቅና ያገኙ 22 ሀገር አቀፍና 54 ክልላዊ በጠቅላላው 76 የፖለቲካ ፓርቲዎች መሆናቸው ይታወቃል። |