|
ቦርዱ ከመገናኛ ብዙሃን ጋር ምክክር አደረገ |
|
|
|
|
ሐምሌ 25 ቀን 2003ዓ.ም
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በመራጮችና በሥነ-ዜጋ ትምህርት አሰጣጥ ላይ ያተኮረና የሕዝቡን ግንዛቤ ለማሳደግ የሚያስችል ከክልል መገናኛ ብዙሃን ጋር ከሐምሌ 22-23 ቀን 2003 ዓ.ም ለሁለት ቀናት በአዳማ ከተማ ያካሄደውን የጋራ ምክክር አጠናቀቀ።
የቦርዱ ሰብሳቢ ክቡር ፕ/ር መርጋ በቃና እንደገለጹት የዚህ ምክክር ዋና ዓላማ መራጩ ህዝብ ስለ ምርጫ በቂ ግንዛቤ እንዲያገኝ ለማስቻል፣ የመራጮች እና የሥነ ዜጋ ትምህርት የተለያዩ የማስተማሪያ ዘዴዎችን በመጠቀም በቅድመ ምርጫ፣ በምርጫ እና በድህረ ምርጫ ወቅቶች ለህብረተሰቡ የማድረስ ኃላፊነት ስላለበት ከመገናኛ ብዙሃን ጋር በትምህርቱ አሰጣጥ ስነ-ዘዴ ላይ ለመምከር ነው ብለዋል።
ቦርዱ ከመደበኛ ሥራው ጎን ለጎን ለሥነዜጋና ለመራጮች ትምህርት ማስተማሪያ የሚሆን ሰነድ ከ2000 ዓ.ም. ጀምሮ ልዩ ትኩረት ሰጥቶ በጥንቃቄ በማዘጋጀትና በአውደ-ጥናት በማጠናከር ለ2002 ጠቅላላ ምርጫ አገልግሎት እንደሰጠ ጠቁመው ትምህርቱ ለህብረተሰቡ የተሻለ እውቀትና ክህሎት በማስጨበጥ ለዴሞክራሲያዊ ምርጫ የበኩሉን አስተዋፅኦ አብረክቷል። በመሆኑም ይህን የሥነ ዜጋና የመራጮች ትምህርት መስጫ ማኑዋል በምርጫ ወቅት የተገኘውን ትምህርትና የሌሎች ሀገሮች ተሞክሮዎች ታክለውበት መዘጋጀቱን ሰብሳቢው ገልፀዋል።
በአሁን ጊዜ የሥነ-ዜጋና የመራጮች ትምህርት ማስተማሪያ ሰነዱ ደረጃውን የጠበቀና ቋሚ የማስተማሪያ ማኑዋል ሆኖ ለአገልግሎት እንዲውል ቦርዱ ማጽደቁን አብራርተዋል፡፡ ስለሆነም የዜጎችን ሥነዜጋዊ እውቀትና ክህሎት በቅድመ ምርጫ፣ በምርጫ እና በድህረ ምርጫ፣ ወቅቶች በቀጣይነት አጠናክሮ ለመስጠት ሁኔታዎች መመቻቸታቸውን ጠቁመዋል። የማኑዋሉ ዝግጅት ጊዜ የወሰደ፣ የጽሕፈት ቤቱ ባለሙያዎችና የቦርዱ አባላት ብዙ የሠሩበት እና በዘርፉ ከፍተኛ ልምድ ያካበቱ የመንግስት እና የግል ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት መምህራን የተሳተፉበትና ደረጃውን በጠበቀ መልኩ ያዘጋጁት የማስተማሪያ ማኑዋል ነው። በቦርዱ ውሳኔ መሠረት ደረጃ በደረጃ ማኑዋሉ በሁሉም የክልል የሥራ ቋንቋዎች በመተርጎም ላይ ይገኛል። በአሁኑ ጊዜ የትርጉም ሥራው በ4 የክልል የሥራ ቋንቋዎች እየተጠናቀቀ ሲሆን አሁን በተዘጋጀው በአማርኛ ቋንቋ ማኑዋል በመጠቀም ትምህርት ስርጭቱን መጀመር እንዲቻል ቦርዱ የሚተላለፍበትን ጊዜ ወስኖ በቅርቡ የሚያሳውቅ መሆኑን ገልፀዋል። በቀጣይም ትምህርቱን ለመራጩ ህዝብ በሚገባው ቋንቋ በተከታታይነት እንደምታደርሱ እምነቴ የላቀ ነው ሲሉ የቦርዱ ሳብሳቢ ክቡር ፕ/ር መርጋ በቃና ለተሳታፊዎቹ እምነታቸውን ገልፀዋል።
በምክክር መድረክ ላይ ሰፊ ወይይት የተካሄደ ሲሆን የትምህርት አሰጣጥ ዘዴው የሁሉንም ክልሎች ባህል፣ ቋንቋና የህብረተሰቡን ግንዛቤ ደረጃ በጠበቀ መልኩ መሆን እንደሚገባው፣ የክልሎቹ ተወካዬች፣ የኢትዮጵያ ሬዲዮና ቴሌቪዥን እንዲሁም የፋና ብሮድካስት ኮርፖሬት ተወካዬች ስምምነት ላይ መድረሳቸው ተውቋል። |