|
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በምርጫ ክልል ማካለል ላይ የሰጠውን ስልጠና በአገሪቱ ለሚካሄደው የማካለል ስራ ትልቅ አስተዋፅኦ እንደሚኖረው የቦርዱ ሰብሳቢ ገለፁ፡፡ የቦርዱ ሰብሳቢ ፕሮፌሰር መርጋ በቃና እንደገለፁት ስልጠናው በምርጫ ክልል ማካለል ዙሪያ መልካም ተሞክሮና እና መሰረታዊ ዕውቀት የተገኘበት በመሆኑ የተገኘውን ዕውቀት ወደ ተግባር በማሸጋገር የበኩላችንን መወጣት ይኖርብናል ብለዋል፡፡
ይህ ስልጠና የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ከ Building Resources in Democracy and Good Governance for Electoral Assistance (BRIDGE) በመተባበር ያዘጋጀው ስልጠና ነው፡፡ በዚህ ስልጠና ላይ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ አባላት፣ የጽ/ቤቱ እና የመምሪያ ኃላፊዎች፣ የቅርንጫፍ ጽ/ቤት ኃላፊዎች፣ ከህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት፣ ከፌዴሬሽን ም/ቤት፣ ከኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን፣ ከእንባ ጠባቂ ተቋም፣ ከፌዴራል ስነ-ምግባርና ፀረ-ሙስና ኮሚሽን፣ የክልሎች እና የከተሞች ርእሰ መስተዳድር ኃላፊዎች፣ ከዘጠኙ የክልል እና ሁለት የከተማ አስተዳድር ምክርቤቶች፣ ከማዕከላዊ ስታስቲክስ ባለስልጣን እና ከኢትዮጵያ ካርታ ስራዎች ኤጀንሲ የተወከሉ አካላት ተካፍለዋል፡፡
ስልጠናው በሁለት ዙር የተሰጠ ሲሆን የመጀመሪያው ዙር በአስተዳደራዊ ጉዳዮች እና በሁለተኛው ዙር በቴክኒካል ስራው ላይ በማተኮር በአጠቃላይ በምርጫ ክልሎች ማካለል መርህ፣ የምርጫ ማካለል ሂደት ፣ በዕቅድ አስተቃቀድ እና የመሳሰሉት እንዲሁም በመልክዓ ምድራዊ የመረጃ ሲስተም (Geographical Information System) ላይ ግንዛቤ ተይዟል፡፡
ስልጠናው አሳታፊ እና በተሞክሮ ላይ የተመሰረተ እንደነበር፣ በቀጣይም ተከታታይነት ያለው ስልጠና መስጠት እንደሚገባ፣ በስልጠናው በተገኘው ዕውቀት በአገራችን ለሚካሄደው የምርጫ ክልሎች በአዲስ መልክ የማካለል ስራ የሚጠበቅባቸውን ሙያዊ እገዛ እንደሚያደርጉ ተሳታፊዎቹ ተናግረዋል፡፡
ስልጠናው በሁለት ዙር ለተከታታይ ሶስት ቀናት የተሰጠ ሲሆን በአንደኛው ዙር 27 በሁለተኛው ዙር 26 በጠቅላላ 53 ሰልጣኞች ተካፍለዋል፡፡
የኢትዮጵያ ብሔራዊ የምርጫ ቦርድ ከያዛቸው ዕቅዶች መካከል የምርጫ ክልል በአዲስ መልክ ማካለል አንዱ ነው፡፡ ይህንን ተግባር በብቃት ለማስፈፀም የተለያዩ የዓቅም ግንባታ ስራዎችን እየሰራ ይገኛል፡፡ በ2003 ዓ.ም በተመሳሳይ መልኩ በምርጫ ክልል የማካለል ስራ ከ Public administration International (PAI) በመተባበር ለአምስት ተከታታይ ቀናት ስልጠና መስጠቱ ይታወሳል፡፡ |