|
ቦርዱ ከሲቪክ ማህበራት ጋር የመራጮችና የሥነ-ዜጋ ትምህርት አስመልክቶ ውይይት አካሄደ |
|
|
|
|
ህዳር 23 ቀን 2004 ዓ.ም
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ለኢትዮጵያ ለሴቶች ፌዴሬሽን፣ለኢትዮጵያ መምህራን ማህበር እና ለአዲስ አበባ ወጣቶች ማህበር ህዳር 21 ቀን 2004 ዓ.ም የአሰልጣኞች ሥልጠና በአዳማ ከተማ መስጠቱን አስታወቀ፡፡
ቦርዱ በተሻሻለው የምርጫ ህግ አዋጅ ቁጥር 532/1999 መሰረት መራጩ ህዝብ ስለምርጫ በቂ ግንዘቤ እንዲያገኝ ለማስቻል የመራጮችና የሥነ- ዜጋ ትምህርትን የተለያዩ ዘዴዎችን በመጠቀም በቅደመ ምርጫ፣ በምርጫ ወቀትና በድህረ ምርጫ መከናወን ስለሚገባቸው ሁኔታዎች ለህብረተሰቡ በማዳረስ ላይ መሆኑ የቦርዱ ሰብሳቢ ፕ/ር መርጋ በቃና አስታውቀዋል ። በዚህ ረገድ ቦርዱ የተለያዩ አበረታች ተግባራትን በማከናወኑ የመራጩ ሕዝብ ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መጥቷል፡፡
በቀጣዩ ዓመት ለሚካሔደው የአካባቢና ለ2007ቱ ጠቅላላ ምርጫ መራጩ ህዝብ በሥነዜጋ ላይ ያለውን ዕውቀት ለመገንባትና የምርጫ ሥርአት በገለልተኝነት ለማስፈጸም ቦርዱ ቅድመ ዝግጅቶችን በማጠናቀቅ ላይ መሆኑን እና መራጩም ህዝብ ስለምርጫ በቂ ዕውቀትና ግንዛቤ እንዲጨብጥ በሚደረገው ጥረት በተለይም የሙያ ፣ የሴቶችና የወጣቶች ማህበራትና ሌሎች የሲቪክ ማህበራት የመራጮችና የሥነዜጋ ትምህርቱን በስፋት በስራቸው ለሚገኙ አባሎቻቸው ለማዳረስና ብሎም ከህብረተሰቡ ዘንድ ግንዛቤ ለመፍጠር ከፍተኛ ሚና እንደሚጫወቱ የቦርዱ ሰብሳቢ ጨምረው አስታውቀዋል ።
ከዚህ ጋር አያይዘውም ለመጀመሪያ ጊዜ ወጥነት ያለው እና ደረጃውን የጠበቀ የመራጮችና የሥነዜጋ ትምሕርት መጽሐፍ አዘጋጅቶ በሁሉም የክልል እና የከተማ አስተዳደሮች የመገናኛ ብዙሃን ማለትም በሬዲዮ ፕርግራም በኩል በተከታታይ ትምሕርቱ ለመራጩ ሕዝብ ከጥቅምት 1 ቀን 2ዐዐ4 ዓ.ም. ጀምሮ በመሰጠት ላይ ይገኛል፡፡ የመራጮችና የሥነዜጋ ትምህርቱን ለማዳረስ በአማራ፣ በኦሮሚያ፣ በትግራይ እንዲሁም በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች አምስት ቋንቋዎች መጽሀፍት ተዘጋጅተዉ መሰራጨታቸዉን ፕሮፌሰር መርጋ የቦርዱ ሰብሳቢ ተናግረዋል ።
ትምህርቱ በተጨማሪ በኢትዮጵያ ሬዲዮ፣ በፋና ብሮድካስት፣ በሁሉም የክልል መገናኛ ብዙሃን በኩል ለመራጩ ህዝብ በማሠራጨት ላይ መሆኑን አስረድተዋል ።በመጨረሻም 66 ተሳተፊዎች ስልጣናውን የተካፈሉ ሲሆን በስልጣናው አቅም የሚፈጥር እውቀት ማግኝታቸውንና መዘጋጀታቸውን ገልፅዋል፡፡ |