|
ለፖለቲካ ፓርቲ ከፍተኛ አመራሮች ስልጠና እየተሰጠ ይገኛል፡፡ |
|
|
|
|
ታህሳስ 3 ቀን 2004 ዓ.ም
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ለፖለቲካ ፓርቲ ከፍተኛ አመራሮች ደብረዘይት በሚገኘው የኢትዮጵያ ሥራ አመራር ኢንስቲትዩት ከታህሳስ 2-6 ቀን 2004 ዓ.ም ጀምሮ ለ5 ቀናት በሚቆይ በሁለንተናዊ ለውጥ አመራር (Transformational Leadership) ሥልጠና በመሰጠት ላይ ይገኛል፡፡
የፖለቲካ ፓርቲዎች አቅም ለመገንባት በሀገራችን የተጀመረውን የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ሂደት በይበልጥ ለማጠናከር እና ወደ ተሻለ ደረጃ ለማድረስ ይህ መድረክ የፖለቲካ ፓርቲዎች ያካበቱትን የተለያዩ ልምድና ሃሣብ የሚለዋወጡበት ነው ሲሉ የቦርዱ ሰብሳቢ ፕ/ር መርጋ በቃና ገልጸዋል፡፡
ቦርዱ ቀደም ሲል በተለያዩ አበይት ጉዳዮች ማለትም በግጭት አፈታት፣ በምርጫ ህግ፣ በተሻሻለው የፓለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባ ህግ እና እነዚህን ህጎች መሰረት በማድረግ በወጡ ደንቦችና መመሪያዎች ዙሪያ ለፖለቲካ ፓርቲ ከፍተኛ አመራሮች ተከታታይነት ያለው የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረኮችን ሲያዘጋጅ መቆይቱን የቦርዱ ሰብሳቢ አክሎ ገልፆዋል፡፡ በመቀጠል ፕ/ር መርጋ ሲናገሩ ከዚህ በፊት ሁለንተናዊ የለውጥ አመራር ሥልጠና ላልወሰዱ የፖለቲካ ፓርቲ ከፍተኛ አመራሮች በሙሉ ሥልጠናው እንደሚቀጥል አስታውሰው፤ ለወደፊትም በተመሳሳይ መልኩ በዐቢይ ሀገራዊ ጠቃሜታ ባላቸው ጉዳዮች በመነሳት ሌሎች ሥልጠናዎች እንደሚያዘጋጅ እና ከፓለቲካ ፓርቲዎች ጋር የዘወትር ግንኙነቱን የበለጠ አጠናክሮ አንደሚቀጥል አስታውቀዋል፡፡
በሌላ በኩል አንዳንድ የሥልጠናው ተሳታፊዎች እንደገለጹት ይህ መሰል ሥልጠና የአመራር ክህሎቶቻችን ከነበረው በተሻለ ደረጃ ከፍ የሚያደረግ እና የውስጥም ሆነ የውጪ አሠራሮቻችን ክህሎት የሚያሳድግ፣ በአመራር ውስጥ የሚኖር የሥራ ግንኙነት ዘመናዊ በሆነ መልኩ የሚቀይር፣ በፓርቲዎች የሚከሰቱ የውስጥም ሆነ የውጪ ግንኙነትን እና በአጠቃላይ ፓርቲዎችንም ሆነ እራሳችን ጭምር እንዴት መምራት እንዳለብን ግንዛቤያችን ወደ ላቀ ደረጃ የሚያጎለብት ሥልጠና መሆኑን ገልጸው፤ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድም እንደከዚህ በፊት ሁሉ ለወደፊትም ያሉብንን የአቅም ክፍተቶች በመፈተሽ የአቅም ግንባታ ሥልጠናዎች ቀጣይነት እንዲኖራቸው ሲሉ ጠይቋል፡፡ ሥልጠናው የፓርቲዎችን ስብጥር ባካተተ መልኩ ለሁለት ዙር የሚሰጥ ሲሆን በአሁኑ ስልጠና የተሳታፊዎች ብዛት ሴት 3 ወንድ 29 በአጠቃለይ 32 ሰልጣኞች ስልጠናውን እየተከታተሉ መሆናቸውን ለማወቅ ተችሏል፡፡፡፡
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ባለፈው ዓመት ከሰኔ 6 ቀን 2003 ዓ.ም ጀምሮ ለከፍተኛ የፖቲካ ፓርቲ አመራሮች በሁለንተናዊ ለውጥ አመራር ላይ በደብረዘይት በሚገኘው የስራ አመራር ተቋም በሁለት ዙር መስጠቱ ይታወቃል፡፡
|