ቌንቌ | Language
     
 
መግቢያ ዜና የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ከፖለቲካ ፓርቲ ከፍተኛ አመራሮች ጋር ውይይትና ምክክር አደረገ ፡፡
     
 
Banner

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ከፖለቲካ ፓርቲ ከፍተኛ አመራሮች ጋር ውይይትና ምክክር አደረገ ፡፡ PDF Print E-mail

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ‹‹ የምርጫ አለመግባባቶች አፈታትና ቅደመ ማስጠንቀቂያ ›› በሚል ርዕስ ከከፍተኛ የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች ጋር በአዲስ አበባ፣ በአዳማ እና ሃዋሳ ከተሞች የጋራ ውይይትና ምክክር አደረገ ፡፡

የቦርዱ ሰብሳቢ ፕሮፌሰር መርጋ በቃና በጋራ የምክክር መክፈቻ ንግግራቸው ላይ እንደገለፁት የሀገራችን ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ባፀደቁት ሕገመንግሥት አገራችን የመድብለ ፓርቲ ሥርዓት እንድትከተል የደነገገ ሲሆን በዚህ መሠረት ዜጎች በነፃነት ተደራጀተው የፖለቲካ አመለካከታቸውን ለሕዝብ በማቅረብ በሚያደርጉት ሰላማዊ ውድድር በሕዝብ ምርጫ የመንግሥት ሥልጣን የሚያዝበት ሥርዓት መዘርጋቱን ገልጸዋል፡፡

ቦርዱ በሕገመንግሥቱ አንቀፅ 1ዐ2 እና በተሻሻለው የምርጫ ሕግ አዋጅ ቁጥር 532/1999 ዓ.ም. መሠረት ምርጫን በገለልተኝነት ለማስፈፀም የተቋቋመ ተቋም ሲሆን ከተሰጡት ዋና ዋና ተግባራት እና ኃላፊነቶች መካከል የፖለቲካ ፓርቲዎችን የመመዝገብ፣ የመከታተል የመደገፍና አቅማቸውን በተለያዩ ሥልጠናዎች ማሳደግ እንደሚገኝ የቦርዱ ሰብሳቢ አስታውሰው፣ ሀገራችን የጀመረችውን የልማት እና የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ አጠናክሮ ለመቀጠል የፖለቲካ ፓርቲዎች ሚና ከፍተኛ መሆኑ ተናግረዋል፡፡ የፖለቲካ ፓርቲዎች የሀገራችንን ተጨባጭ እውነታዎች ከዓለም አቀፍ አጠቃላይ ሁኔታዎች ጋር በማገናዘብ ለሕዝባችን ቀጣይ ሰላም እና ብልፅግና የሚበጁ ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎች በቅርፅ እንዲሁም በፖሊሲ እና ስትራቴጂ አፈፃፀም የሚታዩ ጉድለቶችን በማረም የሚያበረክቱት አስተዋፅኦ ከፍተኛ መሆኑን ጨምረው ፈልፀዋል፡፡

የፖለቲካ ፓርቲዎች የሚጠበቅባቸውን ሚና ሊጫወቱ የሚችሉት የሕዝቡን መሠረታዊ ችግሮች ለመፍታት አልመው ሲመሰረቱና ውስጣዊ አደረጃጀታቸው በጠንካራ መሠረት ላይ ሲገነባ ነው፡፡ በአሁኑ ወቅት በሀገራችን 24 ሀገር አቀፍ እና 51 ክልላዊ በጠቅላላው 75 የፖለቲካ ፓርቲዎች በሕጋዊነት ተመዝግበው በመንቀሳቀስ ላይ የሚገኙ መሆኑን ጠቅሰው ሀገራችን አሁን ካለችበት የእድገት ደረጃ እና ከድህነት ለመውጣት ከሚጠበቅብን ከባድ ኃላፊነት አንፃር የሚጠበቅባቸውን ሚና ለመጫወት ብዙ መስራት እንደሚጠበቅባቸው ፕሮፌሰር መርጋ ተናግረዋል፡፡

በጋራ የውይይት እና ምክክር መድረኩ ላይ ከዩኒቨርስቲ እና ከተወካዮች ምክር ቤት በመጡ ምሁራንና ባለሙያዎች “ የምርጫ ግጭት አፈታትና ቅድመ ማስጠንቀቂያ ” ፣ “ የፖለቲካ ፓርቲዎች አደረጃጀት፣ መብትና ግዴታ ” እና “ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባ አፈፃፀም ” በሚሉ ርዕሶች ላይ ለውይይት መነሻ የሚሆኑ ፅሁፎች ቀርበዋል ፡፡

በቀረቡት መነሻ ፅሁፎች ላይ ሰፊ እና ጥልቅ ውይይት የተደረገ ሲሆን በቀረቡት ሐሳቦች ላይ የጋራ መግባባት ተደርሷል ፡፡ በጋራ ምክክሩ እና ውይይቱ አሳታፊ እና ግንዛቤያቸውን እንዳሰፋላቸው በመድረኩ ላይ የተሳተፉ የፖለቲካ ከፍተኛ አመራሮች ተናግረዋል፡፡

በጋራ ምክክሩ ጥሪ ከተደረገላቸው 75 የፖለቲካ ፓርቲዎች መካከል 66ቱ የተሳተፉ ሲሆን፣ ከእያንዳንዱ የፖለቲካ ፓርቲ ሁለት ሁለት ከፍተኛ አመራሮች የተወከሉ 126 አመራሮች ተሳትፈዋል ፡፡ በአጠቃላይ ከተሳተፉት 126 ከፍተኛ አመራሮች መካከል 120 ወንዶች እና 6 ሴቶች ናቸው ፡፡

 

 

ክልላዊ መረጃ

አዳዲስ ዝግጅቶች

ለጊዜው ምንም ዝግጅት አልተገኘም
 


ኮፒራይት © 2010
የኢትዮጵያ ብሔራዌ ምርጫ ቦርድ