ቌንቌ | Language
     
 
መግቢያ ዜና ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ በደቡብ ክልል ለሚገኙ የሲቪክ ማህበራት አባላት ስልጠና ሰጠ
     
 
Banner

ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ በደቡብ ክልል ለሚገኙ የሲቪክ ማህበራት አባላት ስልጠና ሰጠ PDF Print E-mail

ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ በደቡብ ክልል ለሚገኙ የሲቪክ ማህበራት አባላት ስልጠና ሰጠ

ሃዋሳ ጥቅምት 1/2007 በያዝነው አመት የሚካሄደውን አምስተኛው ዙር ሀገራዊ ምርጫ ነፃ፣ሰላማዊ፣ዲሞክራሲያዊና ፍትሀዊና በሕዝብ ዘንድ ተአማኒ ሆኖ እንዲጠናቀቅ የሚጠበቅባቸውን ሁሉ ለመወጣት መዘጋጀታቸውን የደቡብ ክልል የሲቪክ ማህበራት አባላት አስታወቁ፡፡

በእውቀት ላይ የተመሰረተ ምርጫ በማካሄድ እስካአሁን ከተደረጉት ምርጫዎች በተሻለ ደረጃ ምርጫውን ለማስፈፀም ልዩ ትኩረት መሰጠቱን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ገልጿል፡፡

ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ በደቡብ ክልል ለሚገኙ የሲቪክ ማህበራት ያዘጋጀው የአቅም ገንባታ ስልጠና ትናንት ተጠናቋል፡

ሀገራዊና ክልላዊው ምርጫ ዓለም አቀፍ መርሆዎችን በተከተለና የህዝቡን ተቃባይነት ባረጋገጠ ሁኔታ እንዲካሄድ የሚጠበቅባቸውን የዜግነት ግዴታ ለመወጣት መዘጋጀታቸውን አረጋግጠዋል፡፡

ከስልጠናው ተሳታፊዎች መካከል የከፋ ዞን የሴቶች ማህበር ሰብሳቢ ወይዘሮ ሮዛ ቃሲም እንዳሉት ባለፉት ምርጫዎች ብሄር፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች በነፃነት በመረጧቸው ተወካዮቻቸው አማካኝነት ራሳቸውን በራሳቸው በማስተዳደር ላይ ይገኛሉ።

ለዘንድሮው ምርጭ ፍትሃዊነት ከዝግጅት ጀምሮ እስከፍጻሜውና ከዜጎች ምን እንደሚጠበቅ በቂ እውቀት ያገኘሁበት ስልጠና ነው ብለዋል፡፡

የደቡብ ክልል መምህራን ማህበር ፕሬዜዳት አቶ አማኑኤል ጳውሎስ ስልጠናው ዜጎች ሰብአዊና ዲሞክራሲያዊ መብታቸውንና ግዴታቸውን ጠንቅቀው እንዲያውቁና የዲሞክራሲያዊ ምርጫ ምንነትን በአግባቡ እንዲረዱ የሚያግዝ ነው ብለዋል፡፡

የክልል፣ የዞንና የወረዳ መምህራን ማህበር አመራሮች በስልጠናው መሳተፋቸውን የገለጹት አቶ አማኑኤል ምርጫው ነፃ፣ ፍትሃዊ፣ዲሞክራሲያዊ፣ ሰላማዊና በህዝብ አመኔታ ያለው እንዲሆን ከማህበሩ ምን ይጠበቃል ለሚሉ ጥያቄዎች በቂ ምላሽ ያገኙበት መሆኑን አስታውቀዋል፡፡

የደቡብ ክልል መምህራን ማህበር በ14 ዞኖች፣አራት ልዩ ወረዳዎች፣በ136 ወረዳዎችና 22 የከተማ አስተዳደር የሚገኙ ከ760 የሚበልጡ አመራሮችና ከ80 ሺህ የሚበልጡ መምህራንን የያዘ በመሆኑ በስልጠና ያገኙትን እውቀት እስከታች እንደሚያወርዱ ገልጸዋል፡፡

ማህበሩ ከ80 ሺህ በሚበልጡ መምህራን አማካኝነት ከአራት ሚሊዮን ለሚበልጡ ተማሪዎች የስነ ዜጋና ስነ ምግባር ትምህርት በመስጠት ከባለድርሻ አካላት ጋር በትኩረት እየሰራ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡

ማህበሩ የ2007 ሀገራዊና ክልላዊ ምርጫ ሰላማዊና ፍትሃዊ ሆኖ እንዲካሄድ ሁሉንም አባላት በማሰልጠን በቅርቡ በጂንካ ከተማ በሚደረገው ክልል አቀፍ ጉባኤ ላይ የአሰራር አቅጣጫ ያስቀምጣል ብለዋል፡፡

የሀላባ ልዩ ወረዳ ወጣቶች ማህበር ፀሀፊ ወይዘሮ ታየች ሞላ ምርጫው ነፃና ፍትሃዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ የተለያዩ ማህበራት ሚና ምን መሆን እንዳለበት በውል የተገነዘቡበት ስልጠና መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ዜጎች እውቀትና ግንዛቤ አግኝተው በሀገሪቱ የምርጫ ሂደት ንቁ ተሳታፊ በመሆን ለዲሞክራሲ ስርዓት ግንባታ የበኩላቸውን እስተዋጽኦ ማበርከት የሚችሉበት የአቅም ግንባታ ስልጠና ነው ብለዋል፡፡

በስልጠናው ያገኙት እውቀት ከማህበሩ አባላትና ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር እስከታች በማውረድ ውጤታማ ስራዎች ለማከናወን ዝግጁ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

የኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ፕሮፌሰር መርጋ በቃና ቦርዱ በእውቀት ላይ የተመሰረተ ምርጫ ለማካሄድ እስካአሁን ከተደረጉት ምርጫዎች በተሻለ ደረጃ ቀጣዩን ምርጫ ለማስፈፀም ልዩ ትኩረት መሰጠቱን ገልፀዋል፡፡
ስልጠናው ዜጎች በህገመንግስት፣በዲሞክራሲያዊ ሰርዓት፣በህዝብ የስልጣን ባለቤትነትና ሌሎች ህገ መንግስታዊ መብቶችና ግዴታዎችን ጠንቅቀው በማወቅ ለሰላማዊ ምርጫ እንዲሰለፉ ለማድረግ ነው ብለዋል፡፡

ቦርዱ ከተለያዩ ሲቪክ ማህበራት ጋር ያለውን ግንኙነት የበለጠ በማጠናከር ከአባሎቻቸው ብዛትና ተደራሽነት አንፃር የቀሰሙትን ግንዛቤ እስከታችኛው የህብረተሰብ ክፍል እንዲያወርዱ ለማድረግ እንደሆነ አስታውቀዋል፡፡

ለሁለት ቀን በሃዋሳ ከተማ በተሰጠው የአቅም ግንባታ ስልጠና ላይ በክልሉ ሁሉም ዞኖችና ልዩ ወረዳዎች የሚገኙ የሴቶች፣ የመምህራንና የወጣቶች ማህበር አመራሮች ተሳታፊ ሆነዋል፡፡

 

 

ክልላዊ መረጃ

አዳዲስ ዝግጅቶች

ለጊዜው ምንም ዝግጅት አልተገኘም
 


ኮፒራይት © 2010
የኢትዮጵያ ብሔራዌ ምርጫ ቦርድ