|
የዘንድሮው የመራጮች ምዝገባ ከመቼውም ጊዜ በበለጠ የሕዝቡ ተሳትፎ እየታየበትና በርካታ ሕዝብ እየተመዘገበ የሚገኝበት ነው |
|
|
|
|
ጥር 26 ቀን 2002
የዘንድሮው የመራጮች ምዝገባ ከመቼውም ጊዜ በበለጠ የሕዝቡ ተሳትፎ እየታየበትና በርካታ ሕዝብ ለመራጭነት እየተመዘገበ የሚገኝበት መሆኑን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ አስታወቀ፡፡ ማንኛውም ሕብረተሰብ ለመራጭነት በሚመዘገብበት አካባቢ ስድስት ወር የኖረ መሆኑ ከተረጋገጠ መመዝገብ እንደሚችልም ቦርዱ አመልክቷል፡፡
እስከ ጥር 24 ቀን 2002 ድረስ ከ22 ሚሊዮን በላይ ሕዝብ ለመራጭነት መመዝገቡንም ቦርዱ ገልጿል፡፡ የቦርዱ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ መሐመድ አብድራሕማን እንዳስታወቁት በአሁኑ ወቅት በየምርጫ ጣቢያው ምዝገባው ከተጀመረ ጀምሮ በርካታ ሕዝብ ለመራጭነት እየተመዘገበ ነው፡፡ አስቀድሞ በነበሩት የምርጫ ጊዜያት ሕዝቡ ወደ መጨረሻው የመመዝገቢያ ቀናት ወደ ምርጫ ጣቢያዎች የመምጣት ልምድ ቢኖረውም በአማካኝ በየቀኑ ከአንድ ሚሊዮን በላይ ሕዝብ እየተመዘገበ መሆኑን መረጃዎች እንደሚያመለክቱ ጠቁመዋል፡፡
በአሁኑ ወቅት በመላው አገሪቱ ከ22 ሚሊዮን በላይ ሕዝብ ለመራጭነት መመዝገቡንና ፓርቲዎች ዕጩዎቻቸውን ለሕዝብ ተወካዮችና ለክልል ምክር ቤቶች እያስመዘገቡ ነው ብለዋል። በመሆኑም እስካሁን 47 ፓርቲዎች 864 ተጠቋሚ ዕጩዎችን ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 145 ተጠቋሚ ዕጩዎችን ለክልል ምክር ቤት ማስመዝገባቸውን አስረድተዋል፡፡ ኃላፊው እንዳሉት በግል ደግሞ 37 ግለሰቦች ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ስምንት ለክልል ምክር ቤት ለመወዳደር ተመዝግበዋል፡፡
ከዚሁ ጎን ሕብረተሰቡ በየትኛውም አካባቢ ከመታወቂያ ወረቀት ውጭ እሱነቱን የሚገልጽ የሰው ምስክርና የፅሑፍ ማስረጃ ካቀረበና በመራጭነት ለመመዝገብ የሚያስችለውን ቅድመ ሁኔታ ካሟላ መመዝገብ እንደሚችል አስረድተዋል፡፡ በተጨማሪም ተመዝጋቢው የያዘው መታወቂያ ጊዜ ያለፈበትና የቤት ቁጥር ባይኖረው ምዝገባውን ማካሔድ እንደሚችልና ይህ ሳይሆን ቀርቶ ተመዝጋቢው ችግር ቢደርስበትና መመዝገብ ባይችል በየደረጃው ቅሬታዉን ማቅረብ የሚችልበት አሠራር መዘርጋቱን ጠቁመዋል፡፡ |