|
በአዲስ አበባ የመራጮች ቁጥር ከ600 ሺህ በላይ ደረሰ |
|
|
|
|
ጥር 28 ቀን 2002
አዲስ አበባ ውስጥ የመራጮች ቁጥር ከ600ሺህ በላይ መድረሱን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ አስታወቀ፡፡ በመዲናዊ የተለያዩ ፓርቲዎች 192 ተወዳሪዎችን ማስመዝገባቸውን አስታውቋል፡፡ የቦርዱ የአዲስ አበባ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ጌታሁን ገብረመድኅን እንደገለፁት በከተማዋ ከዕለት ወደ ዕለት የተመዘገቡ መራጮች ቁጥር እየጨመረ መጥቷል፡፡
በተለይም በተያዘው ሳምንት ከመቼውም ጊዜ የበለጠ ሕዝብ ወደ ምርጫ ጣቢያዎች እየሔደ ለመራጭነት የሚያበቃውን ካርድ እየወሰደ መሆኑንና ይህ ሕዝቡ በዲሞክራሲ መብቱ ለመጠቀም ያለውን ተነሳሽነት እንደሚያሳይም ጠቁመዋል፡፡
ለመወዳደር ከተመዘገቡት ዕጩዎች መካከል 178ቱ በተለያዩ 15 ፓርቲዎች የተመዘገቡ ሲሆን ቀሪዎቹ ደግሞ በግል መመዝገባቸውን አስታውቀዋል፡፡
በአሁኑ ወቅት በአዲስ አበባ ደረጃ 50 በመቶ የሚሆነው ሕዝብ የተመዘገበ መሆኑን አመልክተው ካርዱን ያልወሰደው ሕዝብ በቀረው ጥቂት ቀናት ውስጥ ሊመዘገብ እንደሚገባ አስረድተዋል፡፡ ተጠቋሚ ዕጩዎች ካስመዘገቡ ፓርቲዎች መካከል መድረክ፣ ቅንጅት ፣ መላው ኢትዮጵያ ብሔራዊ ንቅናቄ (መኢብን) ፣ መላው ኢትዮጵያውያን ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (መኢዴፓ) ይገኙበታል።
እንዲሁም የኢትዮጵያ የሰላምና የዴሞክራሲ ፓርቲ (ኢሰዴፓ)፣ የኢትዮጵያ ፍትኅና ዴሞክራሲያዊ ኃይሎች ግንባር (ኢፍዴኃግ)፣ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኢብዴፓ)፣ የኦሮሞ ብሔራዊ ኮንግረስ (ኦብኮ)፣ ብርሃን ለአንድነትና ለዴሞክራሲ ፓርቲ (ብለለፓ)፣ የኢትዮጵያ ራዕይ ፓርቲ (ኢራፓ) እና የሶዶ ጎርደና ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ ድርጅት (ሶጎሕዴድ) ሌሎቹ ተጠቋሚ ዕጩዎች ያስመዘገቡ ፓርቲዎች ናቸው።
ከዚህም ሌላ የመላው አማራ ሕዝብ ድርጅት (መአሕድ)፣ ወለንኛ ቋንቋ ተናጋሪ ሕዝቦች ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ወቋተሕዴን)፣ የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት (መኢአድ) እና የትግሪ ወርጂ ብሔረሰብ ዴሞክራሲያዊ አንድነት ፓርቲ (ትወብድአፓ) ተጠቋሚ ዕጩዎቻቸውን አስመዝግበዋል። በአዲስ አበባ በ23 ምርጫ ክልሎችና በ1 ሺህ 717 ምርጫ ጣቢያዎች ምርጫው የሚካሄደው ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ነው። የዚህ ምክንያት ደግሞ በ2000 ዓ.ም የአካባቢና የማሟያ ምርጫ በአዲስ አበባ በመደረጉና 138 መቀመጫዎች ያሉት ምክር ቤት ተቋቁሞ ሥራ በመጀመሩ ነው። |