ቌንቌ | Language
     
 
መግቢያ የምርጫ ታዛቢዎች
     
 
Banner

PDF Print E-mail

የምርጫ ታዛቢዎች


በአገሪቱ የሚካሄዱ ምርጫዎች በገለልተኛ ምርጫ አስፈፃሚዎች ግልጽ፣ ነፃ፣ ዴሞክራሲያዊና ፍትሃዊ በሆነ መንገድ ማከናወን ወሣኝ ነው፡፡ ለዚህም የምርጫ ታዛቢዎች ሚና የጐላ ይሆናል፡፡ የምርጫ ታዛቢዎች በምርጫ ክልሎች እና በምርጫ ጣቢያዎች የምርጫ ሂደትን የሚታዘቡ በተለያዩ አካላት የሚወከሉ ሰዎች ናቸው፡፡ ዋና ተልዕኳቸውም የምርጫውን ታአማኒነት በህዝብ ስም ለማረጋገጥ ነው፡፡

በተሻሻለው የኢትዮጵያ የምርጫ ህግ አዋጅ ቁጥር 532/1999 እንደተደነገገው ምርጫን የሚታዘቡ አካላትን በአራት ከፍሎ ማየት ይቻላል፡፡

እነሱም፡-

1.  የአገር ውስጥ ምርጫ ታዛቢዎች፣

2.  የውጭ አገር ምርጫ ታዛቢዎች፣

3.  የህዝብ ታዛቢዎች፣

4.  የዕጩ ተወዳዳሪ ወኪሎች ተብለው ይጠራሉ፡፡

 

1. የአገር ውስጥ ምርጫ ታዛቢዎች

የምርጫውን ሂደት ለመታዘብ የሚፈልጉ የምርጫ ታዛቢዎች በምርጫ ህጉ አንቀጽ 79፣80 እና 81 የተደነገጉትን ድንጋጌዎች በማሟላት እና ከቦርዱ ፍቃድ በማግኘት ምርጫውን ለመታዘብ ይችላሉ፡፡

 

2. የውጭ አገር ምርጫ ታዛቢዎች

አገሪቱ የተቀበለቻቸው ስምምነቶች እንደተጠበቁ ሆነው መንግሥት አስፈላጊ ሆኖ ሲያገኘው የውጭ ታዛቢዎችን ሊጋብዝ እንደሚችል እና የውጭ የምርጫ ታዛቢ ቦርዱ በሚያወጣው መመሪያ መሠረት በገለልተኝነት፣ የሀገሪቱን ሉአላዊነትና ልዩ ልዩ ህጐችን በማክበር የምርጫውን ሂደት መታዘብ እንደሚችሉ በምርጫ ህጉ አንቀጽ 78/2 እና 81/2 ተደንግጐ ይገኛል፡፡

 

3. የህዝብ ታዛቢዎች

በምርጫ ህጉ መሠረት የምርጫውን አጠቃላይ ሂደት የሚታዘቡ የህዝብ ታዛቢዎች በምርጫ ክልል እና በምርጫ ጣቢያ ይደራጃሉ፡፡ በዚሁ መሠረት የእያንዳንዱ ምርጫ ጣቢያ ኃላፊ ለምርጫ ጣቢያው ህዝብ ይፋ የስብሰባ ጥሪ በማድረግ በህዝቡ፤ ከህዝቡ መካከል አምስት አባላትን የያዘ ኮሚቴ በማስመረጥ የሚያደራጁ ሲሆን በቁጥር ከሶስት የማይበልጡ የምርጫ ክልል የህዝብ ታዛቢዎች ከምርጫ ጣቢያ ህዝብ ታዛቢዎች መካከል እንዲመረጡ ይደረጋል፡፡

የኢትዮጵያ ብሔራዊ የምርጫ ቦርድ " በተሻሻለው የሕዝብ ታዛቢዎች እና የዕጩ ተወዳዳሪ ወኪሎች የአሰራር መመሪያ" ቁጥር 3/2001  ዓ.ም  እንደሚያሣውቀው የሕዝብ ታዛቢዎች ሚና መራጩ ሕዝብ በተወካዮቹ አማካይነት የምርጫውን ሂደት እንዲከታተልና እንዲታዘብ ለማስቻል ነው፡፡

በዚህ የቦርድ አሰራር መመሪያ እንደተገለጸው የሕዝብ የምርጫ ታዛቢዎች የምርጫ ክልሉ ወይም የምርጫ ጣቢያ ሕዝብ ዓይንና ጆሮ በመሆን ያገለግላሉ፡፡ የምርጫ ታዛቢዎች ሁሉንም ሂደትና  ደረጃዎችን ይታዘባሉ፡፡

በየተመረጡበት የምርጫ ጽ/ቤት የምርጫ ጣቢያ በምርጫ አፈፃፀም የጊዜ ሰሌዳ ውስጥ በተጠቀሱት ቀናትና ሰዓታት በመገኘት፡-

  1. በመራጮች ምዝገባ ወቅት፡-

እያንዳንዱ መራጭ በትክክል የዚያ ቦታ ኗዋሪነቱን ማረጋገጥ እና የተመዝጋቢዎቹን ዕድሜ በማጣራት ከአንድ ጊዜ በላይ እንዳይመዘገቡ መከታተል፣

  1. በዕጩዎች ምዝገባ ወቅት፡- የድጋፍ ፊርማ የሰጡ ሰዎችን ትክክለኛነት በማጣራትና አስፈላጊ ድጋፍ በመስጠት መካሄዱን መከታተል፣
    1. በምርጫ ዘመቻ ወቅት፡- የዕጩ ተወዳዳሪዎችን የምርጫ እንቅስቃሴ፣ የዕጩ ተወዳዳሪዎች በምርጫ ሕጉና መመሪያዎች መሠረት መንቀሳቀሳቸውን መከታተል፣
    2. በድምፅ አሰጣጥ ሂደት፡- የምርጫ ጣቢያውን አደረጃጀት፣ የድምፅ መስጫ ወረቀቶችን ቁጥር በመመዝገብ አገልግሎት ላይ የሚውሉትን እና የሚበላሹትን፣ የድምፅ ሰጪዎችን ሥነሥርዓት ከምርጫ ሕጉና ደንቡ ወጣ ያለ አሰራር ካለ ሪፖርት ማድረግ፣ የድምፅ መስጫ ሳጥኖች (ኮሮጆዎች) ቁልፎችን በመቆጣጠርና በመጠበቅ ድምፅ የተሰጠባቸውና የተበላሹ የድምፅ መስጫ ወረቀቶችን በመከታተል የድምፅ መስጫ ወረቀቶች ቆጠራ በትክክል መደረጉን መከታተል፣

በተጨማሪም በታዛቢነት ተመርጠው በምርጫ ጣቢያው መገኘት ከጀመሩበት የእጩዎችና የመራጮች የምዝገባ ቀን ጀምሮ ስለእያንዳንዱ የሥራ ቀን ውሎ በየቀኑ ቃለ ጉባኤ ይፈራረማሉ፡፡ ቅሬታ ካላቸው በዕለቱ ቃለ ጉባኤ ላይ ያሰፍራሉ፡፡

  1. በአቤቱታ ሰሚ ኮሚቴ አባልነት፡- በየደረጃው በሚገኙ የምርጫ ጽ/ቤቶች ለሚነሱ ቅሬታዎች አስተዳደራዊ ውሳኔ የሚሰጥ

ሶስት አባላትን አካቶ በምርጫው ወቅት በሚቋቋም ኮሚቴ ውስጥ ሁለቱ አባላት የሚመረጡት ከህዝብ ታዛቢዎች መካከል

ነው፡፡

 

4. የዕጩ ተወዳዳሪ ወኪሎች

  • በምርጫ ክልሉ በፖለቲካ ድርጅቶች ተወክለውም ሆነ በግላቸው ቀርበው ለመወዳደር የተመዘገቡ ዕጩዎች በወኪሎቻቸው አማካይነት አጠቃላይ የምርጫውን ሂደት የመታዘብ መብት አላቸው፡፡ በዚሁ መሠረት እያንዳንዱ ሰው በሚወዳደርበት ምርጫ ክልል ስር በሚገኙ ምርጫ ጣቢያዎች አንዳንድ ተቀማጭ ወኪል እንዲሁም በምርጫ ክልሉ ውስጥ በመዘዋወር ሂደቱን የሚታዘቡለትን ከአምስት የማይበልጡ ተዘዋዋሪ ወኪሎች መመደብ ይችላሉ፡፡ወኪሎቹ በምርጫ ህጉ እና በቦርዱ የወጡት ደንቦችና መመሪያዎችን ማክበርና በድንጋጌዎቹ መመራት ይበጠበቅባቸዋል፡፡

 

 

 

ክልላዊ መረጃ

አዳዲስ ዝግጅቶች

ለጊዜው ምንም ዝግጅት አልተገኘም
 


ኮፒራይት © 2010
የኢትዮጵያ ብሔራዌ ምርጫ ቦርድ