ቌንቌ | Language
     
 
መግቢያ ምርጫ
     
 
Banner

PDF Print E-mail
ምርጫ

ምርጫ ማለት በየጊዜው ወቅቱን ጠብቆ እንደየአገራቱ ተጨባጭ ሁኔታ የሚካሄድ የህዝብ ተወካዮች የሚመረጡበት፣ በሰላማዊ መንገድ የሥልጣን ሽግግር የሚደረግበት፣ የሕዝቦች ዲሞክራሲያዊ መብት ማለትም የመምረጥ እና የመመረጥ መብት የሚተገበርበት ሂደት ነው፡፡ የተለያዩ የምርጫ ዓይነቶች አሉ፡፡ ከነዚህም ውስጥ አገራችን ኢትዮጵያ የምትከተለው የምርጫ ዓይነት የአብላጫ ድምፅ ስርዓት ሲሆን ከተወዳዳሪዎች ውስጥ አብላጫ ድምፅ ያገኘ ፓርቲ ወይም   የፓርቲዎች ጥምር የአስፈፃሚውን አካል ያደራጃል፣ ይህም ም/ቤት አባላት በህዝብ ተወካዮች ምርጫ ስናየው አብላጫውን  ድምፅ ያገኘ ፓርቲ የአስፈፃሚውን አካል ያደራጃል ማለት ነው፡፡

ምርጫ ለምን ያስፈልጋል?

ማንኛውም ዕድሜው የሚፈቅድለትና በህግ አግባብ የመምረጥ እና መመረጥ መብቱ ያልተገፈፈ ሰው የሚሰጠው ድምፅ ብዙ ጠቀሜታ ያለው ሲሆን ከዚህም ውስጥ ጥሩ ፖሊሲና አሰራር ዘርግቶ ለአገር ጥቅም ቅድሚያ የሚሰጥ፣ በውጭም ሆነ በአገር ውስጥ ፖሊሲ የአገሩን ህዝብ ጥቅም የሚጠብቅ፣ የማይሰጥ ሁል ጊዜ  ለህዝቡ የሚያስብ  እንዲሁም ሙስናን አጥብቆ የሚያወግዝ መንግሥትን ለመመስረት ምርጫ ጠቀሜታ አለው ፡፡ ይህንንም በመገንዘብ ለኔ ይበጀኛል፣ ለአገሬ ጥቅም ይሰራልኛል እና የአገሬን ልማት ያፋጥናል የሚሉትን ፓርቲ ወይም ግለሰብ መምረጥ ከላይ የዘረዘርናቸውን ጥቅሞችን የሚያስገኝ ሲሆን በተቃራኒው ደግሞ በምርጫ አለመሳተፍ /አለመምረጥ / ማለት ባልመረጡት አካል መተዳደር ማለት ነው፡፡ በተጨማሪም ምርጫ ህዝቡ የፈለገውን መንግሥት የማቋቋምና የማይፈልገውን ደግሞ ለማውረድ ይጠቅመዋል

 

በመራጮች ምዝገባ ወቅት መራጮች ሊያውቋቸው የሚገነጥቦች

  1. ማንኛውም ሰው ከአንድ ጊዜ በላይና ከአንድ ምርጫ ጣቢያ በላይ መመዝገብ አይችልም፡፡
  2. የመራጭነት ምዝገባ የሚካሄደው በግንባር በመቅረብ ብቻ ነው፡፡

ለመራጭነት ብቁ የሆነ ዜጋ ማን ነው

  1. ዕድሜው በምዝገባው ዕለት 18ና ከዚያ በላይ የሆነው
  2. ኢትዮጵያዊ የሆነ
  3. የመምረጥ መመረጥ መብቱ በህግ ያልተገደበ
  4. የአእምሮ ህመም የሌለበትና መወሰን የሚችል
  5. በአካባቢው ከ6 ወር ጊዜ በላይ የቆየ

ከሆነ መምረጥ ይችላል፡፡

የምርጫ ምዝገባ

የምርጫ ምዝገባ የሚካሄደው በየአካባቢው በየአንድ ሺህ ህዝብ ብዛት በሚቋቋም የምርጫ ጣቢያ ብቻ ነው፡፡ ከዚህ ውጭ በየቦታው ምዝገባ አይካሄድም፡፡

በመራጭነት ለመመዝገብ ሲሄዱ የሚያስፈልጉ የማንነት ማስረጃዎች

ተመዝጋቢው በሚኖርበት ከተማም ይሁን በገጠር በሚገኙ ቀበሌዎች የሚሰጥ የነዋሪነት መታወቂያ፣ የሠራተኛነት መታወቂያ፣ የተማሪነት መታወቂያ፣ ፓስፖርት ከላይ የተጠቀሰው መታወቂያ በሌለበት ወቅት በቅርቡ ፎቶግራፍ ተደርጐበት የተሰጠው እንደ መንጃ ፍቃድ፣ የመኖሪያ ምስክር ወረቀት፣ ከውትድርና የተገለለበት ሰነድ ወይም በተባበሩት መንግሥታት የተሰጠ የስደተኞች ካርድ የመሳሰሉት የመለያ ማስረጃ ናቸው፡፡ ፓስፖርቱ ወይም መታወቂያው ጊዜ ያለፈበት ቢሆንም እንኳን በመራጭነት ለመመዝገብ ሊያገለግል ይችላል፡፡ ከላይ የተገለፁት ማስረጃዎች በማይኖሩበት ወቅት መዝጋቢዎች መራጩን ለይተው የሚያውቁ ከሆነ በገጠር አካባቢ ሲሆን በባህላዊና በልማዳዊ ዘዴ ተመዝጋቢውን ለመለየት የሚቻልበት ካለ በመራጭነት ሊመዘገብ ይችላል፡፡

የመራጮች መለያ ካርድ

  1. ማንኛውም ለመምረጥ ብቁ የሆነ ዜጋ ሁሉ ለመምረጥ ከተመዘገበ በኋላ የመራጮች መለያ ካርድ ይሰጠዋል፡፡ ይህም ካርድ በድምፅ መስጫ ዕለት የማንነቱ መታወቂያ በመሆን ድምፁን በተመዘገበበት ጣቢያ ለመስጠት ያስችለዋል፡፡

የድምፅ አሰጣጥ ሂደት

  1. በድምፅ መስጫው ዕለት ከጠዋቱ 12 ሰዓት ጀምሮ የድምፅ መስጫ ጣቢያው የሚከፈት ሲሆን ለመምረጥ የተመዘገበ ሰው በተመዘገበበት የድምፅ መስጫ ጣቢያ በመገኘት በሚስጢራዊ ድምፅ አስጣጥ ሥርዓት ይበጀኛል ለሚለው ዕጩ ተወዳዳሪ ድምፁን ይሰጣል፡፡ በዚህም ጊዜ ማንን መምረጥ እንዳለበት ምክር አይሰጠውም፣ ማንን መረጥክ ወይም ማንን ልትመርጥ ነው ተብሎ አይጠየቅም፡፡ ይህም ነው ሚስጢራዊ ድምፅ የሚያሰኘው፡፡
  2. ድምፅ ሰጪ ድምፅ በሚሰጥበት ወቅት በሚፈልገው እጩ ምልክት ትይዩ ባለው ሣጥን የ x ምልክት ያደርጋል፤ በሌላ በኩል ደግሞ ማንበብና መፃፍ ካልቻለ በጣት አሻራ ድምፁን ይሰጣል፡፡ በድምፅ መስጫው ላይ ከተገቢው ምልክት ውጪ ሌላ ጽሁፍ መፃፍ አይፈቀድም፡፡ ስለዚህ ስንመርጥ በጥንቃቄ ምልክት ማድረግ ይገባናል፡፡

የድምፅ ቆጠራ ሂደት

በድምፅ መስጫው ዕለት፡- ድምፅ መስጠት ከተጠናቀቀ በኋላ ከምሽቱ 12 ሰዓት ላይ የምርጫ ጣቢያው ይዘጋና ድምፅ የተሰጠበትና ድምፅ ያልተሰጠበት የድምፅ መስጫ ወረቀት ከተለይቶ በኋላ ለህዝብ ተወካዮች የተሰጠን ድምፅና ለክልል ም/ቤት የተሰጠ ድምፅ በመለየት የቆጠራ ሥራ ይከናወናል፡፡ በሚቀጥለው ቀን የጣቢያው ድምፅ ቆጠራ ውጤት  በምርጫ ጣቢያው ሰሌዳ ላይ ህዝብ እንዲያየው ይለጠፋል፡፡

 

 

ክልላዊ መረጃ

አዳዲስ ዝግጅቶች

ለጊዜው ምንም ዝግጅት አልተገኘም
 


ኮፒራይት © 2010
የኢትዮጵያ ብሔራዌ ምርጫ ቦርድ